ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በአፍሪካ ምድብ ‘A’ ላይ የተቀመጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሴራሊዮን እና ከቡርኪናፋሶ ብሔራዊ ቡድን ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ አዲሱ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የመረጧቸውን ተጨዋቾች ይዘው ዛሬ በአዳማ ዝግጅት ጀምረዋል።
ከሁለት ቀናት በፊት የተመረጡት አዲሱ አሰልጣኝ ለ30 ተጫዋቾች ጥሪ ማደረጋቸው ሲታወቅ በአዳማ ካኖፒ ሆቴል ሪፖርት በማድረግ ዝግጅት እንዲጀምሩ ከቀረበላቸው 30 ተጨዋቾች መካከል በዛሬው የመጀመሪያ ቀን የተገኙት 26 ተጨዋቾች ናቸው ።
በዛሬው ልምምድ አራት ተጨዋችች አልተገኙም። ከነዚህ መሐል አንጋፋው እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ለረጅም አመታት መጫወት የቻለዉና ከአሰልጣኝ ዉበቱ አባተ ጋር በነበረ አለመግባባት ራሱን ከብሔራዊ ቡድን አግልሎ የነበረው ጌታነህ ከበደ ፤የዋልያዎቹ የፊት መሥመር ተጫዋች እና የማሜሎዲ ሰንዳውንስ አቡበከር ናስር ፣ ከረጅም ዓመታት የግብፅ ሊግ ቆይታ በኋላ ዘንድሮ ለመቻል የፈረመው ሽመልስ በቀለ እና የአሜሪካው ሃርትፎርድ አትሌቲክስ ክለብ በቀጣይ የፈንጆቹ የውድድር ዓመት ከዋናው ሊግ ቀጥሎ ለሁለተኛ ዲቪዚዮን በክለቡ የመጫወት ዕድል የሰጠው የፋሲል ከነማው ጋቶች ፓኖም ሲሆኑ ተጨዋቾቹ በቀጣይ ቀናት ቡድኑን ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል።