👇
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ ሰኞ ህዳር 24 2016 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያ(ዎች)ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
በሳምንቱ መርሃግብር በተደረጉ ጨዋታዎች ስድስት በመሸናነፍ ቀሪ ሁለቱ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ 16 ጎሎች በ15 ተጫዋቾች ተቆጥረዋል። 34 ቢጫ ካርድ ለተጫዋቾች ሲሰጥ አራት ቀይ ካርድ ተመዝግቧል ።
በሳምንቱ አራት ተጫዋቾች ላይ የዲሲፕሊን ውሳኔ ተላልፏል። ቴዎድሮስ በቀለ(ሀምበሪቾ) ክለቡ ከ ፋሲል ከነማ ጋር ባደረገው ጨዋታ በ8 ኛ ደቂቃ ላይ የተጋጣሚን ቡድን ግልፅ ግብ ዕድል በማበላሸት ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ ሲሆን ለፈፀመው ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 3 ጨዋታ እንዲታገድና የገንዘብ ቅጣት ብር 3000 /ሶስት ሺ/ እንዲከፍል፣ ተስፋዬ መላኩ(ወልቂጤ ከተማ) ክለቡ ከ ሻሸመኔ ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ በ67 ኛ ደቂቃ ላይ የተጋጣሚን ተጫዋች በመማታት ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ ሲሆን ተጫዋቹ ለፈፀመው ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 4 ጨዋታ እንዲታገድና የገንዘብ ቅጣት ብር 3000 /ሶስት ሺ/ እንዲከፍል፣ ሞሰስ ኦዶ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) ክለቡ ከ ባህርዳር ከተማ ጋር ባደረገው የ6ኛ ሳምንት እግርኳስ ጨዋታ በ7 ኛ ደቂቃ ላይ የተጋጣሚን ተጫዋች በመማታት ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ ሲሆን ተጫዋቹ ለፈፀመው ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 4 ጨዋታ እንዲታገድና የገንዘብ ቅጣት ብር 3000 /ሶስት ሺ/ እንዲከፍል እንዲሁም ግሩም ሃጎስ(መቻል) ክለቡ ከ ኢትዮጵያ መድን ጋር ባደረገው እግርኳስ ጨዋታ በ 76 ኛ ደቂቃ ላይ የተጋጣሚን ቡድን ግልፅ ግብ የማግባት ዕድል በማበላሸት ከጨዋታ ሜዳ ሲሆን ለፈፀመው ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 3 ጨዋታ እንዲታገድና የገንዘብ ቅጣት ብር 3000 /ሶስት ሺ/ እንዲከፍል ተወስኗል።
በስድስት ክለቦች ላይም የተለያዩ የዲሲፕሊን ውሳኔዎች ተላልፏል። መቻል(አራት ተጫዋቾች)፣ አዳማ ከተማ(አምስት ተጫዋቾች)፣ ባህርዳር ከተማ(ስምንት ተጫዋቾች)፣ ወልቂጤ ከተማ(አራት ተጫዋቾች) በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት የተጠቀሱት ክለቦች የገንዘብ ቅጣት ብር 5,000 /አምስት ሺ/ እንዲከፍሉ ተወስኗል፡፡ በተጨማሪም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከባህርዳር ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የእለቱ ዳኞችን አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸውና የውሀ መጠጫ ፕላስቲክ ጠርሙስ ወደሜዳ ስለመወርወራቸው ሪፖርት የቀረበ ሲሆን የክለቡ ደጋፊዎች አፀያፊ ስድብ በመሳደባቸው በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መሠረት ብር 50,000 /ሀምሳ ሺህ/ እንዲሁም ቁሳቁስ ወደ ሜዳ በመወርውራቸው በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሠረት ብር 25,000 /ሀያ አምስት ሺህ / በድምሩ ክለቡ ብር 75,000/ሰባ አምስት ሺህ/ እንዲከፍሉ ፣ አዳማ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበረው ጨዋታ የክለቡ ደጋፊዎች የዕለቱ ዳኞችን አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸው ሪፖርት የቀረበበት እና ደጋፊዎች ከዚህ በፊት አፀያፊ ስደብ በመሳደብ ከተቀጡት ቅጣት ሊታረሙ ባለመቻላቸው በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት አዳማ ከተማ ብር 75,000 ሰባ አምስት ሺህ / እንዲከፍል እንዲሁም የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችም የራሳቸውን ቡድን ተጫዋቾችና የቡድን አመራሮች አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸው ለመደባደብና የሀይል ጥቃት ለማድረስ ስለመሞከራቸው ሪፖርት የቀረበ ሲሆን የክለቡ ደጋፊዎች በተደጋጋሚ አፀያፊ ስደብ በመሳደብ ከተቀጡት ቅጣት ሊታረሙ ባለመቻላቸው በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ኢትዬጵያ ቡና ብር 100,000 አንድ መቶ ሺህ / እንዲከፍል ተወስኗል።