ዜናዎች

#የአሜሪካው Hartford Athletic ክለብ የዋልያዎቹ አንድ ተጨዋችን በእጁ አስገብቷል –

 

 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሐምሌ 23/2015 ወደ አሜሪካ ካመራ በኋላ ማረፊያውን በቨርጂንያ ስተርሊንግ ሆሊዴይ ኢን ሆቴል ቆይታ በማድረግ ሁለት የወዳጅነት ጨዋታ አድርጎ ሁለቱንም በማሸነፍ የአሜሪካ ጉዞውን አጠናቆ ነገ ወደ ሀገሩ ይመለሳል።

ብሔራዊ ቡድኑ በአሜሪካ ቆይታው የመጀመርያ ጨዋታውን ሐምሌ 26 ከጉያና ብሔራዊ ቡድን ጋር አከናውኖ በአንጋፋውና አምበሉ ሽመልስ በቀለ ባስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች ተጋጣሚውን የጉያና ቡድንን 2 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል። በተመሳሳይም ከትላንት በስቲ ከላውደን ዩናይትድ  ክለብን ደግሞ 4 ለ 2 አሸንፈዋል።
በጨዋታው ላይ ለብሔራዊ ቡድን ተጠርተው ወደ አሜሪካ ካመሩት ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች መካከል ግብ ጠባቂው ዳንኤል ንጉሤ እና የመስመር ተጫዋቹ ማርከስ ቬላዶ ፀጋዬ ለመጀመርያ ጊዜ ተሰልፈው ጥሩ እንቅስቃሴ አድርገዋል። በተለይም ግብ ጠባቂው ዳንኤል ንጉሤ የፍፁም ቅጣት ምት በመመከት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ አሳይተዋል።

 

ከጨዋታው በተጨማሪም በስፍራው የነበሩ የዲሲ ዩናይትድ ክለብ መልማዮች እና ሌሎች መልማዮች ጨዋታው ላይ ተገኝተው የተጫዋቾችን እንቅስቃሴ በመመልከት የሚፈልጓቸውን ተጨዋቾች በማነጋገር በአሜሪካ እንዲቀሩ በማድረግ ላይ መሆናቸው ከስፍራው ለኢትዮ ኪክ የደረሰን የታማኝ ምንጭ መረጃ  ማስነበባችን ይታወሳል።

ታማኝ ምንጮች ለኢትዮኪክ ጨምረው እንደገለፁት  ከዋናው ከአሜሪካ ሜጀር ሊግ ቀጥሎ በሁለተኛ ዲቪዚዮን (USL Championship ) የሚጫወተው ሃርትፎርድ አትሌቲክስ የተባለው እና ሌላኛው የሁለተኛ ዲቪዚዮን ክለቦች  የብሔራዊ ቡድኑ ተጨዋቾችን ማነጋገራቸው ታውቋል።    በተለይ ሃርትፎርድ አትሌቲክስ ክለብ ሲሆን ሁለት የዋልያዎቹ ተጨዋቾች አሜሪካ እንዲቀሩ ከትላንት ጀምሮ ጥረት እያደረጉ ሲሆን ፌዴሬሽኑ ተጨዋቾቹ ከኢትዮጵያ ክለቦቻቸው ጋር ያላቸውን የኮንትራት ጊዜ በሚል አዲስ አበባ ደርሰው እንዲመለሱ በማለት አለመፍቀዱን መረጃዎች ጠቁመዋል።
ይሁንና ዛሬ ፌዴሬሽኑ ከዋልያዎቹ ለአንዱ ተጨዋች ከክለቡ ጋር ኮንትራቱ በመጠናቀቁ አሜሪካ እንዲቀር የተፈቀደለት ሲሆን Hartford Athletic ከተባለው ክለብ ጋርም ይኸው ተጨዋች ለአንድ ሳምንት የሙከራ ጊዜ ተሰጥቶቷል።


በአንፃሩ ዕድሉን Hartford Athletic ክለብ ያገኘው ሌላኛው ተጨዋች ከክለቡ ጋር የአንድ ዓመት ኮንትራት በመኖሩ ሊሳካለት ባይችልም፣ ተጨዋቹ አዲስ አበባ ከሚገኘው የክለቡ ፕሬዚዳንት ጋር በመደወል የአሜሪካ ዕድሉን ለማሳካት ጥረት ላይ መሆኑን መረጃው ያመለክታል።

በተመሳሳይ  ዲሲ  ዮናይትድና ሌላኛው የሁለተኛ ዲቪዚዮን ክለብ አራት የዋልያዎቹ ተጨዋቾች ላይ ከፍተኛ ፍላጎት በማሳየት ተጨዋቾቹን ማነጋሩ ታውቋል። ኢትዮኪክ  ነገ የተጨዋቾቹን ስም ዝርዝር ይፋ የምናደርጎ ይሆናል።