ዜናዎች

የቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስ ክለብ የ16ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ለ7ኛ ጊዜ አንስተዋል!

በደማቅ ስነ ስርዓት ፍፃሜውን ባገኘው 16ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ቅዱስጊዮርጊስ (ፈረሰኞቹ ) በደጋፊዎች የደመቀ ህብረ ዝማሬ በመታጀብ የዋንጫ ተጋጣሚውን መቻልን በመደበኛ ጨዋታ ባስቆጠሩት ብቸኛ ግብ 1 ለ 0 በማሸነፍ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል ።

የ16ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ የተዘጋጀለትን ልዩ ዋንጫና የወርቅ ሜዳሊያ ከዕለቱ የክብር እንግዳ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ ከአቶ አብርሀም ታደሰ እጅ ተቀብለዋል ።

 

 

በሁለተኛና ሶስተኛነት ያጠናቀቁት መቻልና ኢትዮጵያ ቡና የብርና የነሀስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሁነዋል።

የዕለቱ የጨዋታ ኮኮብ የሆነው 10 ቁጥር ለብሶ የተጫወተውና ድንቅ ብቃቱን ያሳየው የቅዱስጊዮርጊሱ ሀብቶም ገ/እግዚያብሄር የ10ሺህ ብርና ሌዩ ዋንጫ ሽልማት አግኝቷል::

በዕለቱ ጨዋታውን በብቃት የመሩ ዳኞች ዋና ዳኛ ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማን ጨምሮ ልዩ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል ።

መስከረም 7/2015ዓ.ም በ6 ክለቦች መካከል በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታድየም ሲካሄድ የሰነበተው 16ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ #ሲቲ_ካፕ ዛሬ ፍፃሜውን ሲያገኝ ቅዱስ ጊዮርጊስ አንደኛ ሲያጠናቅቅ ኢትዮጵያ ቡና እና መቻል ሁለተኛና ሶስተኛ በማድረግ ፍፃሜውን አግኝቷል።

የቅዱስጊዮርጊስ ደጋፊዎች፣ የመቻል ደጋፊዎ፣ የስፖርት ቤተሰቦች ጨምሮ በአበበ ቢቂላ በስቴዲየም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገኝተው ጨዋታውን የታደሙ ሲሆን ልዩ ድምቀትና ውበት ሆነው አምሽተዋል ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ በተለይ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር በነበራቸው ቆይታ በየአመቱ የሚካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የመዲናችን መለያና ትልቅ ውድድር መሆኑን ገልፀው ይህን ውድድር ወደፊት ደረጃውን በማሳደግ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚገኙ ክለቦች ጭምር የሚሳተፋበትና በአፍሪካ ደረጃ በጉጉት ከሚጠበቁ ውድድሮ አንዱ ለማድረግ ቢሮው ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

አቶ አብርሀም የእግር ኳስ ስፖርት ወንድማማችነት ፣ አንድነት ፣ ፍቅርና ኢትዮጵያዊነት መገላጫ መሆኑን 16ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በተግባር አሳይቷል ሲሉ ገልፀዋል ።

የቢሮው ሀላፊ በንግግራቸው አያይዘውም ለ16ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በቅድመ ዝግጅት ፣ በተግባር የውድድር ወቅት ( ከጅማሮ እስከ ፍፃሜ ) መሳካት አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት በሙሉ ምስጋናቸውን በታላቅ አክብሮት በመግለፅ በቀጣይም የከተማችንን የእግር ኳስ ስፖርት ትንሳኤ ለማስቀጠል እጅ ለእጅ ተያይዘን እንሰራለ ብለዋል ።

#@ገባው የአዲስ አበባ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት