ዜናዎች

“ዓላማችን እንደ የልጅ ልጄ ዴቪ ሴልኬ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣቶችን ለአውሮፓ ክለቦች ማፍራት ነው” – አቶ ሳሙኤልን ባአምና

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን   ነዋሪነቱን ጀርመን ሀገር ካደረገ 3 points ከተባለ ድርጅት ጋር በተለያዩ የዕድሜ ክልል ወጣቶችን በእግርኳስ በማሰልጠን ለብሔራዊ ቡድን እንዲሁም ለአውሮፓ ክለቦች ገበያ ለማብቃት በማሰብ የወጣቶች ብሔራዊ አካዳሚ በቋሚነት ለመገንባት ይፋዊ ስምምነት አድርገዋል። በፊርማው ስነስርዓት ላይ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በኩል ፕሬዚዳንቱ አቶ ኢሳያስ ጅራ እና ዋና ፀሀፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን እንዲሁም በ3 point National Academy Project በኩል መስራቹ አቶ ቴዎድሮስ ሳሙኤል እና ወላጅ አባቱ አቶ ሳሙኤል  ባአምና እንዲሁም ወላጅ እናቱ ተገኝተዋል።

 

አቶ ቴዎድሮስ ሳሙኤል እና አቶ ኢሳያስ ጅራ

 

ከፊርማ ስነስርዓቱ በፊት በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በኩል  ፕሬዚዳንቱ አቶ ኢሳያስ ጅራ  ” የፌዴሽኑ የረጅም ጊዜ ህልም አሁን እውን ሆኗል ” በማለት ሰለ ፕሮጀክቱ ውጪ ገልጸዋል ። አቶ ኢሳያስ ውጪውን በተመለከተ አጠቃላይ ግንባታው ከ6 እስከ 8 ሚሊዮን ብር እንደሚሸፍን ጠቅሰው የግንባታውን ወጪ በተመለከተም አራት አራት ሚሊዮን ሁለቱም አካላት ለማዋጣት መስማማታቸው ተናግረዋል። አቶ ኢሳያስ የተጨዋቾች የዝውውር ፓሊሲ በተመለከተ ታዳጊዎች በአካዳሚው ስኬታማ መሆን ከቻሉ እና ለአውሮፓ ክለቦች የመጫወት ዕድል ከተፈጠ ከሚገኘው ዝውውር ፌዴሬሽኑ 40% እንዲሁም 3 points 60 % እንደሚወስዱ ጠቅሰው አካዳሚው በቅርቡ ለመገንባት ጨረታዎች ይፋ ሆነው ስራው ለመጀመር መታቀዱን ገልጸዋል።
በመቀጠል በጀርመን ቡንደስሊጋው ተጫውቶ ስኬታማ ተጨዋች የነበረው እና በአሁኑ ሰዓት ለጀርመኑ ሄርታ ቢኤስሲ የፊት ለፊት ተጫዋች ሆኖ የሚጫወት የትውልደ ኢትዮዽያዊው ዴቪ ሴልኬ ወላጅ አባት እና የ3 Points National Academy Project መስራች አቶ ቴዎድሮስ ሳሙኤል ራሱን በማስተዋወቅ የፕሮጀክቱን አጠቃላይ ዓላማ አብራርቷል። የፌርማ ስነስርዓቱ ከመካሄዱ በፊትም የአካዳሚው ዲዛይን ለዕይታ በቅቷል።
በስፍራው የተገኘችው የኢትዮ ኪክ የፕሮጀክቱ ጠንሳሽ ከሆኑት እና የቤተሰቡ ዋና የሆኑትን የአቶ ቴውድሮስ ወላጅ አባትን ትውልደ ኢትዮጵያዊውን አቶ ሳሙኤልን ባአምና አነጋግረናል ።
አቶ ሳሙኤልን ባአምና
ኢትዮ – ኪክ :- ብዙዎች የልጅ ልጆትን ትውልደ ኢትዮጵያውን ዴቪ ሴልኬን በጀርመን ሊጎች ሲጫወት ያውቁታል እና እስቲ በቅድሚያ እርሶ እና ቤተሰቦን ቢያስተዋውቁን ?
አቶ ሳሙኤል :- እሺ… አንዳልሽው ብዙዎች የልጅ ልጄን ዴቪ ሴልኬ በተለያዩ የጀርመን ቦንድስሊካ ክለቦች ሲጫወት በስኬታማነቱ እና አሁንም በመጫወት ላይ ያውቁታል ። እንግዴ ዴቭ የልጅ ልጄ ነው።ዴቪ ማለት የመጀመሪያ ልጄ የቴዎድሮስ ልጅ ነው። እኔ አያቱ ነኝ። አራት ወንዶች ልጆች አሉኝ። መላ ቤተሰቡ የሚኖረው ጀርመን ሀገር ነው።ባለቤቴ ወ/ሮ አለሚቱ ትባላለች።
እግርከኳስ በጣም ቤተሰቡ ውስጥ የሚወደድ ነው። አራቱም ወንዶች ልጆቼ ኳስ ከልጅነታቸው ጀምሮ እዛው ጀርመን አካዳዎች ይጫወቱ ስለነበረ ከኳስ ሜዳ ጠፍቼ አላውቅም ብል ይቀላል። በአብዛኛው ጊዜ የማሳልፈው ኳስ ሜዳ ላይ ነው። እናም ሁሌም እመኝ የነበረው  የታዳጊዎች አካዳሚ በአገሬ ቢኖር የሚል ስሜት ነበረኝ።
ይሄ ስሜት የተፈጠረው ከልጅነታቸው ጀምሮ ልጆች በአካዳሚ ሲጫወቱ እና ስኬታማ ሲሆኑ አይ ስለነበረ ምኞቴ በአገሬም ላይ ቢኖር የሚል  ነው።
እንደውም የልጅ ልጄ መነሻው ከልጅነቱ ጀምሮ ከአካዳሚ ሆኖ በቦንድስ ሊጋ ስኬታማ በመሆን ከሚሊዮን ዮሮ በላይ ዝውውር ማግኘት እንዲችል መሠረቱ የወጣቶች አካዳሚ ስለነበር ምኞቴ የነበረው ሀገሬ ላይ ምን አለ እንደዚህ ቢኖር እል ነበር። እግዚአብሔር ይመስገን አሁን ይኸው በእኛ 3 points project ለማሳካት ኢትዮጵያ መጥተናል። ምንም እንኳ ኑሯችን ጀርመን ቢሆንም ይህን ፕሮጀክት ለማሳካት ኢትዮጵያ ለመኖር አስበናል።
ኢትዮ – ኪክ :- ስለ 3 Points National Academy Project ጠቅለል ባለ መልኩ ይንገሩኝ?
አቶ ሳሙኤል:- የ 3 points ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ የሚገኙ በ15፣ 17 እና 20 ዓመት የሚገኙ ታዳጊሚዎችን በማሰልጠን እና ለብሔራዊ ቡድን፤ አልፎም ለታላላቅ የአውሮፓ ክለቦች ገበያ ለማብቃት በማሰብ የወጣቶች ብሔራዊ አካዳሚ መገንባት ነው። ይህ አካዳሚ በርካታ ሚሊዮን ብር ኢንቨስት የሚደርግ ሲሆን ቦታው የካፍ አካዳሚ በሚባለው ቦታ አካባቢ ሲሆን በሚቀጥለው ሳምንት ውስጥ ቦታው ለጨረታ ይቀርባና ስራዎቹ ይጀምራሉ። በእኛ ዕቅድ የአካዳሚዉ ግንባታ በሁለት እና በሶስት ወራት የሚያልቅ ይሆናል።
የ3 point National Academy Project መስራቾች አቶ ቴዎድሮስ ሳሙኤል ፣ከወላጅ አባቱ እና ወላጅ እናቱ ጋር
ኢትዮ – ኪክ :- ስለዚህ የመጀመሪው ተግባራችሁ የሚሆነው ?
አቶ ሳሙኤል :- ተጫዋቾችን ከየክፍለሀገሩ በመመልመል ወደ አዲስ አበባ በማምጣት በሚገነባው አካዳሚ በማቀፍ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ ስልጠናዎችን በመስጠት ታዳጊዎቹን በማብቃት ወደ አዉሮፓ ሊጎች በሚገኙ ክለቦች የሚጫወቱበትን ዕድል መፍጠርን ግብ አድርጎ የተነሳው ጉዳይ ነው ።
ኢትዮ – ኪክ :- በመጀመሪያ ጊዜ የምትቀበሉት ምን ያህል ወጣቶች እና የዕድሜ ገደቡ ?
አቶ ሳሙኤል :- ለመጀመሪያ ጊዜ አሁን ያሰበውነው እስከ 100 የሚሆኑ ዕድሜያቸው ከ15-17 ዕድሜ ያሉትን ነው። ይህም በሁለት ዓመት ከተቻለ ለታዳጊ ቡደን ለአፍሪካ ዋንጫ እንዲጫወቱ እና እነዚህ ልጆች ችሎታው እየዳበረ ሲሄድ ወደ አውሮፓ ክለቦች የሚጫወቱ ዕድል መፍጠር ነው ዋናው የእኛ ግብ አድርገን የተነሳው ። እኛም ኢንቬስት የምናደርገው ገንዘባችን ስለሆነ 24 ሰዓት ከእነሱ ጋር ነው የምንሆነው እንጂ ዝም ብሎ አይደለም። ምክንያቱም ገበሬ ዘር ሲዘራ አይቶ ነውና  ፍሬ ያፈራል ብሎ ነውና   የሚዘራው ፣ የእኛም ልክ እንደ ገበሬው ነው።
ኢትዮ – ኪክ :- ፕሮጀክቱ ውጤታማ ይሆናል ብለው በሙሉ ልብ ያምናሉ ?
አቶ ሳሙኤል :- አዎ። 100 ፕርሰንት ውጤታማ ይሆናል ብዬ ነው የምለው። ምንም ጥያቄ የለኝም ። ምክንያቱም ፕሮፌሽናል የሆኑ እና በዚህ ሙያ ዕውቀት ያላቸውን ይዘን በቅንጅት ነው የምንሰራው ። ሁሉንም ነገር ዘመናዊ በሆነ እና በተቀናጀ መልኩ ለመስራት ተቀናጅተናል። አሁን ቀጣይ ጉዞ ንድፈ ሐሳቡን ወደ ተግባር መለወጥ የሚለው ነው ።የእኛ ትልቁ ዓላማችን እንደ ልጅ ልጄ ዴቪ ሴልኬ ከ120 ሚሊዮን ህዝብ በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮዽያውያን ወጣቶች ለአውሮፓ ክለቦች ማፍራት ነው። ይህንንም እናደርጋለን የሚል ነው።
ኢትዮ – ኪክ :- ለምታስቡት ፕሮጀክት እንደችግር ሊያጋጥመን ይችላል ብላችሁ የምትሰጉት ነገር ይኖር ?
አቶ ሳሙኤል :- የመጀመሪያ ላይ ትንሽ ችግር ሊፈጥር የሚችለው ምናልባት Scouting ሊሆን ይችላል። ተጫዋቾችን ከየክፍለሀገሩ በመመልመል ወደ አዲስ አበባ የማሞጣቱ ሂደት ቢሆንሞ ይህን ለማሳካት ከውጭ አገር የሚመጡ መልማዮች አሉ በተጨማሪም ከሀገር ውስጥ ካሉት ጋር በቅንጅት የታሰበው ይሳካል የሚል እምነት አለኝ።በርግጥ ነው ትንሽ ጊዜ ይፈልጋል።
ኢትዮ – ኪክ :- አካዳሚው ከተሰራ በኋላ የስልጠና ዕቃዎች ፣ትጥቆች እና ከዚህ ጋር የተያዙ ነገሮች ከውጭ የምታስገቡት ?
አቶ ሳሙኤል :- አዎ! ከግንባታው መጠናቀቅ በኋላ ሁሉም ነገሮች ከውጪ የሚገቡ ናቸው። የአካዳሚው አጠቃላይ የመገልገያ ዕቃዎች ሆነ የልጆቹ ትጥቆች ከውጭ ነው። ስለዚህ ይሄ እንግዲህ በእኛ በኩል ብቻ ሳይሆን ከአገሪቱ መንግስትም ጋር ትብብር ይጠይቃል።
ኢትዮ – ኪክ :- በመጨረሻ የሚሉኝ ነገር ካለ ?
አቶ ሳሙኤል : የምለው ቢኖር – አገራችንን ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይጠብቃት። “እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ ጠባቂ በከንቱ ይደክማል እንሚባለው” እግዚአብሔር አገራችን ሰላም ያድርግልን።