ዜናዎች

” አገሬን ብሎም የተወለድኩባትን ከተማ ማገዝ በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ” ፉዓድ ኢብራም

የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የድሬዳዋ ከነማ ተጫዋች የነበረው ፉዓድ ኢብራም የድሬዳዋ ስታዲየም የምሽት ውድድሮችን በጥራት እና የምሽት ጥላ ሳይኖር ጨዋታዎች እንዲታዮ የሚችሉ ኤል ዲ ፖውዛ ከድባይ በማስምጣት ለከተማው አስተዳደር ዛሬ አበርክቷል።
በአሜሪካ ኑሮውን አድርጎ የነበረውና  ለአሜሪካ ከ17 አመት እና 20 ዓመት በታች ቡድኖች በአለም አቀፍ ውድድሮች በመሣተፍ እንዲሁም በአውሮፖ በተለያዩ ሊጎች የተጫወተው የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋች ፉአድ ኢብራሂም ይህን ድጋፍ  አስመልክቶ ጠይቀነው የሚከተለውን ምላሽ  ኢትዮኪክ ሰጥቶናል ” አገሬን ብሎም የተወለድኩባትን ከተማ እንደዚህ ባሉ ትላልቅ ስፖርታዊ ውድድሮች ላይ በወሳኝ ጊዜ ማገዝ በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ። ወደፊትም ለአገሬ በምችለው መልኩ ለመደገፍ የተቻለኝን አደርጋለው” ብሏል።
እ.ኤ.አ በ2013 አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ወደ አፍሪካ ዋንጫ ጉዞ ውስጥ በነበረው ስብስብ አንዱ የነበረው ፉአድ በወቅቱ የኢትዮጵያ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ይረዳው ዘንድ ከታንዛኒያ አቻቸው ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም ባደረገው የወዳጅነት ጨዋታ ኢትዮጵያ ታንዛኒያን 2ለ 1 ስታሸንፍ ተጨዋቹ የመጀመሪያውን የብሔራዊ ቡድን ጎሉን አስቆጥሯል።
በአሁን ሰአት ኑሮውን በአገር ቤት ላደረገው ፉአድ  ዘንድሮ በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማለፉን አስመልክቶ የተሰማውን  ለጠየቅነው  ሲመልስ ” ኢትዮጵያ አገሬ በትልቅ መድረክ ዳግም ስትመለስ በማየቴ ትልቅ ኩራት እና ትልቅ ነገር ነው። በጣም ደስ ብሎኛል” በማለት ምላሹን የቀደሞ የዋልያዎቹ ተጨዋች ፉአድ ኢብራሂም ሰጥቷል።