Ethiopian Football Team in USA 2023
ዜናዎች

#በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአሜሪካ ቆይታ ዙርያ አጠቃላይ መረጃዎች!

 

– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሐምሌ 23/2015 ወደ አሜሪካ ካመራ በኋላ ማረፊያውን በቨርጂንያ ስተርሊንግ ሆሊዴይ ኢን ሆቴል ቆይታ በማድረግ ላይ ይገኛል።

– ትውልደ ኢትዮጵያዊው ባለሀብት ኢዮብ ማሞ (ጆ ማሞ ካቻ) ከጉያና ጋር ከተደረገው ጨዋታ አንድ ቀን አስቀድሞ ለብሔራዊ ቡድናችን አባላት የእራት ግብዣ ያከናወኑ ሲሆን የድርሻ ባለቤትነት የገዙበት ዲሲ ዩናይትድ ክለብን እና ስታዲየሙን እንዲጎበኝ አድርገዋል። ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች በዲሲ ዩናይትድ የመጫወት እድል እንዲያገኙ እንደሚደረግም ቃል ገብተዋል።

– ብሔራዊ ቡድናችን በአሜሪካ ቆይታው የመጀመርያ ጨዋታውን ሐምሌ 26 ከጉያና ብሔራዊ ቡድን ጋር አከናውኖ ከምርጥ የጨዋታ እንቅስቃሴ ጋር ሽመልስ በቀለ ባስቆጠራቸው ጎሎች 2-0 አሸንፏል።

– ከጉያና ጋር የተደረገው ጨዋታ 5000 ተመልካች በሚይዘው ሴግራ ፊልድ ላይ የተከናወነ ሲሆን 2640 ተመልካች ትኬት ቆርጦ በመግባት ጨዋታውን ተከታትሏል።

– ከጉያና ጋር ከተደረገው ጨዋታ 260 ሺህ ዶላር ገቢ መገኘቱን የጉዞው አዘጋጅ ተቋም አሳውቆናል።

– በጨዋታው ላይ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ እና የመስሪያ ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተው ጨዋታውን በክብር እንግድነት ጨዋታውን በማስጀመር ተከታትለዋል።

– ኢትዮጵያ በአሜሪካ የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ስፖንሰር የሆነው ካፒቶል ፔትሮልየም ባለቤት ኢዮብ ማሞ (ጆ ማሞካቻ) በክብር እንግድነት ተገኝተው ጨዋታውን ከክቡር አምባሳደሩ ጋር በጋራ በማስጀመር ተከታትለዋል።

– ጆ ማሞ ካቻ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ስፖንሰር ከመሆናቸው በተጨማሪ የቡድኑ የተለያዩ ወጪዎችን በመሸፈን ለቆይታው መሳካት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

– በጨዋታው ከኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተመልካቾች በተጨማሪ የቀድሞ የዋልያዎቹ ተጫዋቾች፣ ታዋቂ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እና ጋዜጠኞች ተገኝተዋል።

– የዲሲ ዩናይትድ ክለብ መልማዮች ጨዋታው ላይ ተገኝተው የተጫዋቾችን እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።

– ቡድናችን ለቀጣይ ጨዋታዎች በሴግራ ፊልድ ልምምዱን የቀጠለ ሲሆን ወደ አትላንታ ተጉዞ ከአትላንታ ሮቨርስ ጋር ሊያደርገው የነበረው ጨዋታ የማይካሄድ በመሆኑ በቀጣይ ከሎዶን ዩናይትድ ጋር የሚጫወት ይሆናል።

– ሎዶን ዩናይትድ በአሜሪካ የሊግ መዋቅር በሁለተኛው እርከን ላይ (UCL Championship) የሚወዳደር ሲሆን በዲሲ ዩናይትድ መጋቢ ቡድንነት ከተመሰረተ በኋላ በአሁኑ ወቅት ራሱን ችሎ በመቋቋም በአሜሪካ ውድድሮች ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።

– ክለቡ 5000 ተመልካች የመያዝ አቅም ያለው ሴግራ ፊልድ ስታዲየም ባለቤት ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአሜሪካ ቆይታው ለልምምድ እና ጨዋታዎች እየተጠቀመበት ይገኛል።

– ብሔራዊ ቡድናችን የሚያደርገው ጨዋታ ቅዳሜ ሐምሌ 29 በሴግራ ፊልድ 11:00 AM ላይ (በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ምሽት 12:00) ይከናወናል።

– ለብሔራዊ ቡድን ተጠርተው ወደ ስፍራው ካመሩት ተጫዋቾች በተጨማሪ ለመጀመርያ ጊዜ ጥሪ ተደርጎላቸው በአሜሪካ ቡድኑን የተቀላቀሉት ግብ ጠባቂው ዳንኤል ንጉሤ እና የመስመር ተጫዋቹ ማርከስ ቬላዶ ፀጋዬ በነገው ጨዋታ ላይ የመጫወት እድል ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

– የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በብሔራዊ ቡድኑ የአሜሪካ ቆይታ ጨዋታ ከማድረግ ባሻገር የማልያ ሽያጭ በማከናወን ላይ ይገኛል። (ማልያ ለመግዛት beymart app)

– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዲሲ ዩናይትድ ጋር ጨዋታ እንዲያከናውን ጥረት በመደረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን አዳዲስ ነገሮችን በቀጣይ የሚያሳውቅ ይሆናል።

➡በብሔራዊ ቡድኑ የአሜሪካ ጉዞ ላይ ወደ ስፍራው ያመሩት ዮሴፍ ታረቀኝ እና ብርሃኑ በቀለ ከጉያና ጋር ከተደረገው ጨዋታ አስቀድሞ በመደባደባቸው በዲሲፕሊን ጉድለት ወደ ሀገር ቤት ተመልሰዋል