አቤል ያለው በዘንድሮው የ2016 የኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ የውድድር አመት የአንደኛ ዙር ላይ በ15 ጨዋታዎች ስምንት ግቦችን በማስቆጠር ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ግብፁ ZED Fc ክለብ ተዘዋውሯል።
ኢትዮጵያዊው አጥቂ አቤል ያለው አዲሱን ክለብ ከተቀላቀለ በኋላ ከሊጉ መሪ ENPPI ጋር ዛሬ ወሳኝ ጨዋታ ላይ ተቀያሪ ዝርዝር ውስጥ ገብቶ የመጀመርያ የሊጉን ጨዋታውን ባይሰለፍም ታድሟል። ክለቡ በዚህ ጨዋታ በጭማሪ ደቂቃ በተቆጠረበት ጎል 1 ለ 0 ተሸንፎ በ26 ነጥብ የሊጉ መሪ ከሆነው ENPPI ዝቅ ብሎ በ21 ነጥብ የሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የኢትዮ ኪክ አድሚን ማርታ በላይ ከዛሬው ጨዋታው በፊት ከአቤል ጋር ቆይታ አድርጋለች።
።
ኢትዮኪክ:- በግብፅ ከአዲሱ ክለብህ ጋር እንዴት ነው?
አቤል:- እግዚአብሔር ይመሰገነው በጣም አሪፍ ነው፣ አዲሰ እንደመሆኔ ከቲሙ ጋር እየተላመድኩ እገኛለሁ።
ኢትዮኪክ:- አዚህ የሊጉ የጎል መሪነት በአንደኛ ዙር አንተ ላይ ነው ያቆመው፣ እንዴት ነው ጎል ማምረቱን በግብፅ ለመቀጠል ምን ያህል አቤል ዝግጁ ነው?
አቤል:- ያው እንግዲህ አዲስ ሊግ ከመሆኑ አንፃር መላመድ አለብኝ። እንደሚታወቀው የግብፅ ሊግ ከአፍሪካ ጠንካራ ሊጎች አንዱ ነው። ከእኛ ሀገር ሊግ ደግሞ በጣም የተለየ ነው። እናም የምፈልገውን ለማሳካት ጠንክሬ እየሰራሁ ነው።
ኢትዮኪክ:- ከዚህ ቀደም በምኞት ደረጃ በውጭ አገር መጫወት የምትሻው ክለብ ነበረ ?
አቤል:- በዛ ደረጃ በርግጥ ውጭ ሀገር ሊጎች ላይ በፕሮፌሽናል ወጥቼ መጫወቱን እንጂ በክለብ ደረጃ አስቤ አላውቅም።
ኢትዮኪክ:- የአቤል ወደ ግብፅ መዘዋወርህ ፈረሰኞቹን ይጎዳል እንዲሁም ካላቸው ደረጃ እና ውጤት ይቀንሳል የሚሉ ወገኖች አሉ፣ አንተ በዚህ ላይ ምን ትላለህ ?
አቤል:- ኸረ …ቅ/ጊዮርጊስ በእኔ ወደ ግብፅ መዘዋወር ምንም አይጎዳም። እንደውም በጣም ብዙ አቅም ያላቸው ወጣት ተጨዋቾች አሉ። እንደውም እነዚህ ተጨዋቾች የመሠለፍ ዕድል ያገኛሉ። በይበልጥም ራሳቸውን የሚያሳዮበት ጊዜያቸው ይሆናል ። እናም በእኔ እምነት ምንም አይጎዳም።
ኢትዮኪክ:- የአቤል ቀጣይ የ2024 ዕቅዱ ምን ይሆናል
አቤል:- ያው ዕቅዴ ከፈጣሪ ጋር መጀመሪያ ራሴን ያለኝን አቅም በደንብ ማሳየት እፈልጋለሁ።
ኢትዮኪክ:- ባለቤትና ልጅም አብረው መጥተዋል?
አቤል :- ቤተሰቦቼ የቀጣይ ዓመት እዚህ እንዲመጡ ያሰብኩት። ስለዚህ ይመጣሉ ።
ኢትዮኪክ:- ቡድናቹ ውስጥ የሌላ ሀገር ተጨዋቾች ብዙ አሉ?
አቤል:- ከእኔ ጋር ስምንት የውጭ ሀገር ተጨዋቾች አሉ
ኢትዮኪክ:- የምትለብሰው የማሊያ ቁጥር ?
አቤል:- የሚለብሰው 28 ቁጥር ነው ሁሉም ቁጥሮች ተይዘዋል …በፈገግታ
ኢትዮኪክ:- ከአዲሱ ክለብ ጋር የስኬት ጊዜ እንዲሆንልህ እንመኛለን።
አቤል:- በጣም አመሠግናለሁ ።