የፊታችን ማርች 30/2024 በሰርቢያ ቤልግሬድ ለሚካሄደው በ45ኛው ዓለም አትሌቲክስ አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የሚካፈለው የልዑካን ቡድን ዛሬ በቤለቪው ሆቴል ተሸኘ ::
በመርሀግብሩ መጀመሪያ የቡድኑ መሪና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ዶ/ር ተስፋዬ አስግዶም ስለቡድኑ አጠቃላይ ቆይታቸው የወሰዱት የአካል እና የስነልቦና ስልጠና ለውጤታማነት እንደሚያበቃቸው በመተማመን መልካም እድል ለቡድኑ ተመኝተዋል ።
አትሌቶችን በመወከል ደሞ አትሌት ለምለም ንብረት እና አትሌት ታደሰ ወርቁ የነበራቸውን የስልጠና እና የሆቴል ቆይታ ጥሩና ደስተኛ እንደነበሩ በመግለፅ የኢትዮጵያ ህዝብ ፀሎት ከእኛ ጋር አይለየን ከፈጣሪ ጋር በጥሩ ውጤት እንመጣለን ብለዋል ።
አሰልጣኞችን በመወከል ረ/ኮ አሰልጣኝ ሁሴን ሺቦ ስለነበራቸው የስልጠና ቆይታቸው ጥሩ እደነበረ እና የሰራነው ስራ ከአለም አንደኛ ለመውጣት ነው ከፈጣሪ ጋር ከአለም አንደኛ ወጥተን በደመቀ ሁኔታ እንደምትቀበሉን ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል ።
በመቀጠልም የቡድኑ ቴክኒክ መሪና የኢ.አ.ፌ የተሳትፎና ውድድር ዳይሬክተሩ አቶ አስፋው ዳኜ ሰለ አትሌቶች አመራረጥ ፣ስለ ልምምድ ቦታ እና ስለነበራቸው ስልጠና ሰፊ ማብራሪያ ስጥተዋል።
በዚህ የሽኝት መርሀግብር ላይ የእለቱ የክብር እንግዳ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚ/ር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ክብርት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፣ የመዝጊያ ንግግር ፣ የመልካም ምኞት መግለጫ እና የስራ መመሪያ በመስጠት የሰንደቅ ዓላማ ርክክብ ተደርጓል ።
በዚህ መርሃግብር ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀ/ምክ/ፕሬዝዳንት አትሌት ገዛኸኝ አበራ ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ እንግዳ፣ ታዋቂ አትሌቶች ፣ አሰልጣኞች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
@EAF