ዜናዎች

በሃገራችን ስፖርት ጋዜጠኝነት ውስጥ ትልቅ ቦታ የነበረው ታላቅ ሰው ገነነ መኩሪያ(ሊብሮ) አረፈ !

በሃገራችን ስፖርት ጋዜጠኝነት ውስጥ ትልቅ ቦታ የነበረው  ስፖርት ጋዜጠኛ እና ተንቀሳቃሹ ቤተ መፅሐፍት ፣እግር ኳስ ተጫዋች ፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ(ሊብሮ) ማረፉን ሰማን።   ገነነ ከቅርብ ወራቶች በፊት ከህመሙ ጋር በተያያዘ እግሩን ማጣቱ ቢሰማም ከህመሙ ጋር ትግል እያደረገ ባለበት ሰዓት ዛሬ ጥር 14 ቀን 2016 ዓ.ም ንጋት ላይ ህይወቱ ማለፉ ተሰምቷል። 
ስፖርት ጋዜጠኛ እና ተንቀሳቃሹ ቤተ መፅሐፍት ገነነ የብዙ የስፖርት ስብዕናዎችን ታሪክ የሰነደበት ባለ ቡኒ ቀለም ፊደሎች ጋዜጣ መስራችና ባለቤትም ነበር:: የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቢፈለግ የማይገኙ የሃገሪቱ የእግር ኳስ እውነታዎች ታሪኮች ቁጥሮች እሱ ጋ ተሰንደዋል:: ለወጣት ጋዜጠኞች የሚያውቀውን ከማጋራት ወደ ሗላ የማይል ሰው ነበር ገነነ::
በያዝነው መንገድ የትም አንደርስም ኢትዮጵያዊ እግር ኳስ አጨዋወት መከተል አለብን ብሎ የአሰለጣጠን መመሪያ መጽሐፍ ፅፏል ያመነበትን ሃሳብ ለማሳመን ሲሞግትም ኖሯል:: ከስፖርቱ አድማስ ውጪም ተነግረው የማይጠገቡ ታሪኮችን የሰነደ ጨዋታ አዋቂ ተንቀሳቃሽ ቤተ መጽሐፍት ገነነ መኩሪያ:: ሁለገብነቱ ያስቀናል የስፖርት እውቀቱ ያስገርማል:: ሙዚቃ ላይ ያለው ግንዛቤ ይኼን ሁሉ እንዴት አወቀው ያስብላል::
‘ኢህአፓና ስፖርት’ በደርጉ ዘመን የነበረ የኢትዮጵያን ስፖርት ፖለቲካና አኗኗርን ግልፅ አድርጎ ያሳየበት መፅሐፉ ለብዙዎች የዛ ዘመን ታሪክ ማጣቀሻ ነው:: ‘የነገን አልወልድም’ የሚለው የአብርሃም ገዛኸኝ ድንቅ ፊልም ታሪክ ከገነነ መጽሐፍ የተወሰደ ነው::
ፈጣሪ ነፍስህን በአፀደ ገነት ያኑርልን ለቤተሰቡ እና ለወዳጆቹ መፅናናትን እንመኛለን።