ቤትኪንግ ፕሪሜር ሊግ ዜናዎች

#የሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎች ዳኛን አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸው በቀረበ ሪፖርት /ሃምሳ ሺህ/ ብር ቅጣት ተጥሎባቸዋል!

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2015 24ኛ ሳምንት በሃዋሳ ከተማ በተደረጉ ጨዋታዎች አምስት ጨዋታዎች በመሸናነፍ ሶስት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ 12 ጎሎች በ10 ተጫዋቾች ተቆጥረዋል።የጎሎቹ አገባብም 10 በጨዋታ ሁለት በፍፁም ቅጣት ምት ነው። በሳምንቱ 26 ተጫዋቾችና የቡድን አመራሮች በቢጫ ካርድ ሲገሰፁ አንድ ተጫዋች ቀይ ካርድ ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ ሐሙስ ግንቦት 10 2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያ(ዎች)ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
በተጫዋችና ቡድን አመራሮች ደረጃ በተላለፉ ውሳኔዎች 4 ተጫዋችና ላይ ቅጣት ተላልፏል። አስናቀ ተስፋዬ(ለገጣፎ ለገዳዲ)፣ ሄኖክ አርፍጮ(ሀድያ ሆሳዕና)፣ ብርሀኑ በቀለ(ሀዲያ ሆሳዕና) እና በረከት ሳሙኤል (ሃዋሳ ከተማ) በተለያዩ 5 ጨዋታዎች የቢጫ ማስጠንቅቂያ ካርድ በመመልከታቸው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 1500 /አንድ ሺ አምስት መቶ/ እንዲከፍሉ ፥ ፍሬዘር ካሳ(ሀዲያ ሆሳዕና) በ24ኛ ሳምንት ጨዋታ የተጋጣሚን ቡድን ግልፅ ግብ ዕድል በማበላሸት ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ ስለመሆኑ ሪፖርት የቀረበበት ለፈፀመው ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 3 ጨዋታ እንዲታገድ ና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 3000 /ሶስት ሺ/ እንዲከፍል ተወስኗል።
በክለቦች ደረጃ በታዩ ሪፖርቶችም የተለያዩ ውሳኔዎች ተላልፈዋል። ሀዋሳ ከተማ በሳምንቱ ጨዋታ የተጋጣሚ ክለቡ ደጋፊዎችን እና የእለቱን ዳኛ አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸው ሪፖርት የቀረበ በመሆኑ የክለቡ ደጋፊዎች ለፈፀሙት ጥፋት ክለቡ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ብር 50000/ሃምሳ ሺህ/ እንዲከፍል ፥ አዳማ ከተማም የክለቡ ደጋፊዎች 2/ሁለት/ የሃዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታድየም የተመልካች መቀመጫ ወንበሮችን ስለመስበራቸው ሪፖርት የቀረበ በመሆኑ ክለቡ የተሰበሩትን ወንበሮች እንዲያሰራ ወይም የዩኒቨርስቲው አሰተዳደር የሚያቀርበውን የንብረትን ዋጋ እንዲከፍል ተወስኗል፡፡ በተጨማሪም ለቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ የቡድን መሪ እና ምክትል አሰልጣኝ አዲስ ወርቁ ፣ ለሀዋሳ ከተማ ክለብ የቡድን መሪ እና የደጋፊ ማህበር ተወካይ እንዲሁም ለሲዳማ ቡና ክለብ የቡድን መሪ እና የደጋፊ ማህበር ተወካይ በቀጣይ ቀናት ውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ ለማነጋገር ጥሪ አድርጎላቸዋል።