የ2015 የቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከተጀመረ 5ኛ ሳምንቱ ላይ ይገኛል። ፈረሰኞቹ እስከ አሁን የተደረጉትን ጨዋታዎች በማሸነፍ በመሪነት ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ፈረሰኞቹ በአራት ጨዋታዎች አስራ አምስት ጎሎችን የተጋጣሚ መረብ ላይ በማስቆጠርና ሦስት ኳሶች በተቃራኒ ቡድን ተቆጥሮባቸው በአስራ ሁለት ነጥብ በመያዝ የደረጃ ሰንጠረዡን አናት ተቆናጥተው ይገኛሉ፡፡
በወቅታዊ አቋምና ለቀጣይ ጨዋታ እየተደረገ ስላለው ዝግጅት የልሳነ-ጊዮርጊስ ከአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ጋር አጠር ያለች ቆይታ አድርጋለች።
ልሳነ-ጊዮርጊስ፡- የባህርዳር ቆይታችሁ የተመቻችሁ ይመስላል እስኪ ስለ ቆይታችሁ ንገረኝ?
ዘሪሁን ሸንገታ፡- የባህርዳር ቆይታችን በጣም አሪፍ ነው፤ አቅደን የመጣነውን እቅዳችንን እያሳካን ስለሆነ በጣም አሪፍ ነው፡፡
ልሳነ-ጊዮርጊስ፡- እስከ አሁን አራት ጨዋታዎችን አድርጋችሁ ሁሉንም በአሸናፊነት አጠናቃችኋልና ጨዋታዎች እንዴት ነበሩ?
ዘሪሁን ሸንገታ፡- እስከ አሁን ያደረግናቸው ሁሉንም ጨዋታዎች በድል ተወጥተናልና በጣም አሪፍ ነበር፤ በጥሩ ስነ-ምግባር ተጫውተንና መጫወት ባለብን የጨዋታ ዘይቤ አከናውነን የተሻለ ውጤት በአራቱም ጨዋታዎች ማስመዝገብ ችለናል፡፡
ልሳነ-ጊዮርጊስ፡- የባህርዳር የመጨረሻውን ጨዋታ ከፋሲል ጋር ታደርጋላችሁና በልጆቹ ዘንድ ያለው የማሸነፍ ስነ-ልቦና ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
ዘሪሁን ሸንገታ፡- በልጆች ዘንድ ያለው የአሸናፊነት ስነ-ልቦና በጣም አሪፍ ነው፤ ከአሁን በፊት ያደረግናቸውን አራቱንም ጨዋታዎች በጥልቅ የማሸነፍ ስነ-ልቦና በጠንካራ ስራ ነው ማሸነፍ የቻልነውና በተጨዋቾች ዘንድ ያለው የአሸናፊነት መንፈስ በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡
ልሳነ-ጊዮርጊስ፡- ለጨዋታው እያደረጋችሁት ያለው ዝግጅትስ ምን ይመስላል?
ዘሪሁን ሸንገታ፡- በጨዋታው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ሁሌም እንደምናደርገው ሁሉ ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን በጥሩ የማሸነፍ ስነ-ልቦና ላይ እንገኛለን፡፡
ልሳነ-ጊዮርጊስ፡- ከጨዋታውስ ምን እንጠብቅ?
ዘሪሁን ሸንገታ፡- ሁሌም ወደ ሜዳ የምንገባው በአሸናፊነት መንፈስ ነው ፣ስለዚህም የለመድነውን ይዘን ከሜዳ እንወጣለን ።
ልሳነ-ጊዮርጊስ፡- ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ በየጨዋታው ጎል እያስቆጠረ ይገኛልና ምስጢሩ ምን ይሆን?
ዘሪሁን ሸንገታ፡- ጥልቁ ምስጢሩ ስራና ስራ ነው፤ጥሩ ጥሩ ልጆች ስላሉን ኳስን እንደ ቡድን እንዲጫወቱ በማድረግና እንደ አስልጣኝ የምሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት በአግባቡ ስለሚወጣ ነው እንደዚሁም እንደቡድን መንቀሳቀስ በመቻላችን ከዚህም በላይ ብዙ ጎሎችን ማስቆጠር ይችላል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም አሁን በቡድናችን ውስጥ ያለው የተጨዋቾች ጥራት ሆነ ወቅታዊ አቋም ልጁ ከዚህ በላይ ማድረግ እንደሚችል ጥሩ እድል የሚሰጥ ነው ፡፡
ልሳነ-ጊዮርጊስ፡- ከተጨዋቾች ጉዳት ጋር በተገናኘስ ምን አዲስ ነገር አለ?
ዘሪሁን ሸንገታ፡- ዳዊት ተፈራ ከአዳማ ከተማ ጋር ከነበረን ጨዋታ በፊት በልምምድ ላይ በአጋጠመው ጉዳት ለስድስት ሳምንታት ከሜዳ ይርቃል፡፡ ከሱ ውጪ ያሉ ሁሉም ተጨዋቾች ሙሉ ጤንነት ላይ ይገኛሉ አቤል ያለውም ቢሆን ልምምድ እየሰራ ይገኛል፡፡
ልሳነ-ጊዮርጊስ፡- ለደጋፊዎቻችን ማስተላለፍ የምትፈልገው መልዕክት ካለህ እድሉን ልስጥህ
ዘሪሁን ሸንገታ፡- ደጋፊዎቻችን ማመስገን እፈልጋለሁ አሁን ላይ እያስመዘገብነው የምንገኘው ውጤት የሁላችንም የጋራ ጥረት በመሆኑ ደጋፊዎቻችን ሁሌም እንደሚያደርጉት ሁሉ ከጎናችን በመቆም የማይነጥፍ ድጋፋቸውንና ፍቅራቸውን እስከ መጨረሻው እንዲለግሱን ማለት እፈልጋለሁ ።