ዜናዎች

የኢትዮዽያ ቡናው ታፈሰ ሰለሞን በዲሲፕሊን ግድፈት ከቡድኑ ተለይቶ ሸገር ይገኛል!

በ2013 ዓ.ም የቤት ኪንግ ፕሪሚየር ሊግ በ 41 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ የውድድር አመቱን የጨረሰው እና በ2014 በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ማጣሪያ ላይ ኢትዮጵያን በመወከል የተሰለፈው ኢትዮጵያ ቡና የዘንድሮው የቤትኪንግ አጀማመሩ ቀዝቀዝ ያለ ይመስላል።

ቡድኑ በ2014 የቤትኪንግ በአራት ሳምንታት ጨዋታ ሁለቱን ሲሸነፍ ሁለቱን ያለ ጎል ባዶ ለባዶ በማጠናቀቅ በደረጃ ሰንጠረዡ ከመጨረሻው አንድ ደረጃ ከፍ ብሎ በ15ኛ ደረጃ ይገኛል።

በአንፃሩ ለኢትዮጵያ ቡና በ2013 በ29 ጎሎች ኮከብ ግብ አስቆጣሪ የነበረው አቡበከር ናስር ዘንድሮ ጅምሮው እንደ ባለፈው አመት ባለመሆኑ ቡድኑ የጎል ድርቀት አጋጥሞቷል ማለት ይቻላል። በርግጥ ሊጉ ገና በጅማሮ ላይ ከመሆኑ አንፃር ቡድኑ ክፍተቶቹን ለማስተካከል በቂ ጊዜ ስላለው በቀጣይ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ለቡድኑ ምላሽ ይሰጡታል ተብሎ ይጠበቃል።

በተያያዘ መረጃ የኢትዮጵያ ቡና የመሐል ሜዳ ተጨዋች ታፈሰ ሰለሞን በዲስፕሊን ግድፈት ከቡድኑ ተለይቶ አዲስ አበባ ሪፖርት ለማድረግ መምጣቱ ታውቋል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ተጨዋቹ ከመጠጥ ጋር በተያያዘ በልምምድ ሜዳ አለመገኘቱ ሲሰማ ይህንንም ለክለቡ ሪፖርት እንዲያደረግ በታዘዘው መሠረት አዲስ አበባ እንደሚገኝ እና ከሪፖርቱ በኃላ ሃዋሳ ወደ ቡድኑ እንደሚመለስ ታውቋል።

የቀድሞ የኒያላ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሀዋሳ ከተማ አማካይ ታፈሰ ቡናማዎቹን ከተቀላቀለበት ጊዜ አንስቶ ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደነበር አይዘነጋም።

የኢትዮጵያ ቡና አማካኝ ታፈሰ ሰለሞን በቡናማው መለያ እስከ ሰኔ 30 /2016 ዓ.ም የሚያቆውን የውል ስምምነት ዘንድሮ ማደሱ ይታወሳል።