ዜናዎች

” የዋንጫ ጨዋታ ለመዳኘት በመመረጤ በጣም ደስ ብሎኛል ፣ እግዚአብሔርን ማመስገን እፈልጋለሁ ” ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ

በግብፅ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲካሄድ የነበረውን የአፍሪካ የሴቶች የቻምፒየንስ ሊግ ነገ ፍፃሜ ሲያደርግ የፍፃሜ ጨዋታውን ኢትዮዽያዊቷ ብቸኛዋ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ በዋና ዳኝነት የምትዳኘው መሆኑ ታውቋል።

የደቡብ አፍሪካው የሴቶች ሊግ ሻምፒዮን ማሜሎዲ ሰንዳውንስ በካፍ የሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ከጋናዊው ሃሳካስ ኤፍሲ ጋር ነገ አርብ ምሽት የፍፃሜ ጨዋታ ያደርጋሉ።

ስኬታማዋና ብዙም ያልተዘመረላት ኢትዮጵያዊቷ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ የነገውን የመጀመሪያ የአፍሪካ የክለቦች የፍፃሜ ጨዋታን መዳኘቷ የፈጠረባትን ስሜት አሰመልክቶ  ለኢትዮኪክ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥታናለች

ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ

 

” በቅድሚያ እግዚአብሔርን ማመስገን እና ክብሩንም ለእሱ ሰጥቻለሁ። በጣም ደስ ብሎኛል ። ” ካለች በኃላ የካፍ የመክፈቻ ጨዋታዎችንና የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎችን በብቃት የመራችው ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ስለ ነገው ጨዋታ ቀጥላ ስትናገር

“ይህ የአፍሪካ የሴቶች የቻምፒየንስ ሊግ የመጀመሪያ እንደመሆኑ መጠን ይህን የዋንጫ ጨዋታ ለመዳኘት በመመረጤ በጣም ደስ ብሎኛል። በድጋሚ እግዚአብሔርን ማመስገን እፈልጋለሁ። እንኳን እኔ ብቻ አይለይም አንችም መላው ኢትዮጵያዊ ደስ ይለዋል። እግዚአብሔር ታላቅ ነው። ሁሉም በጊዜ እና በሰዓት ሆኗል ” በማለት ምላሿን ሰጥታለች።

የነገው ማሚሎዲ ሰንዳዉ እና ሀሳካስ የአፍሪካ የሴቶች የቻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ምሽት ሁለት ሰዓት የሚደረግ ይሆናል።