ዜናዎች

” ሰባት ቋሚ ተሰላፊዎቻችን በብሔራዊ ቡድን በመሆናቸው በዛሬው ጨዋታ ባይሰለፉም ጨዋታው ለቀሪ አባሎቻችንን መልካም አጋጣሚ ነው ” – አሰልጣኝ ስዩም ከበደ

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ
ለአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ከሳምንታት በኋላ ኢትዮጵያን በመወከል የሚያደርገው የአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ፋሲል ከነማ ለዝግጅቱ ይረዳው ዘንድ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ዛሬ ከቀኑ በ10:00 ሰዓት በአሰልጣኝ ሰርዲዮቪች ሚሉቲን  ሚቾ ከሚሰለጥነው ዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የሚያደርጉ ይሆናል።
የ2013 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮናው የፋሲል ከነማ ስፓርት ክለብ በቀጣይ ለሚጠብቀው ሀገራዊ እና የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ አዲስ እና ነባር ተጨዋቾችን በመያዝ ዝግጅቱን ከሳምንታት በፊት መጀመሩ ይታወሳል።
የፋሲል ከነማ ስፓርት ክለብ በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታውን መስከረም 2/2014 ዓ.ም ከሱዳኑ አል-ሂላል ጋር በባህርዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም የሚያደርግ ሲሆን የመልሱን ጨዋታ በሳምንቱ ሱዳን ካርቱም መስከረም 9/2014 የሚደርጉም ይሆናል። የዛሬውን ጨዋታ እንዲሁም የቡድኑ አብዛኞቹ ተጨዋቾች በብሔራዊ ቡድን ግዴታ ላይ መሆናቸው ለክለቡ የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የሚያስከትለውን ጫና በተመለከተ የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ስዩም ከበደን ኢትዮኪክ በመጠየቅ ምላሽ ሰጥተዋናል።
የፋሲል ከነማ ስፓርት ክለብ
በቅድሚያ ከዮጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚያደርጉት የወዳጅነት ጨዋታ ለቡድናችው ያለውን ጠቃሚታ አሰልጣኝ ስዩም ሲናገሩ “የዝግጅት ልምምድ መለኪያዉ የወዳጅነት ግጥሚያ ነዉ ፥ ምንም እንኳን ሰባት ቋሚ ተሰላፊዎቻችን በብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ላይ በመሆናቸው በዛሬው የወዳጅነት ጨዋታ ባይሰለፉም በአንፃሩ ይህ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ለቀሪ አባሎቻችንን የምናይበት መልካም አጋጣሚ በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው” ብለዋል።
በቀጣይ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የቡድኑ ቋሚ ተሰላፊዎች በብሔራዊ ቡድን ግዴታ ላይ መሆናቸው እና የጨዋታ መቀራረብ በቡድኑ ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ በተመለከተ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ በተመለከተ ሲናገሩም ” ትልቁም ፈተና እዚህ ላይ ነዉ። በጥቅሉ መስከረም 2/2014 ዓ.ም ባህርዳር ላይ የሱዳኑን አል-ሂላል ጋር ከመጫወታችን 2 ቀን ሲቀረዉ ብቻ ነዉ ልጆቻችንን የምናገኜዉ እናም ይበልጥ በስነልቦናዉና በራስ የመተማመን መንፈሳቸዉን በማነሳሳት በጠንካራ ተፎካካሪነት ስሜት በሜዳችን ተጠቃሚ ለመሆን አስፈላጊዉን ሁሉ እናደርጋለን ብየ እጠብቃለሁ” በማለት አሰልጣኝ ስዩም ለኢትዮኪክ ምላሽ ሰጥተዋል።