የኢፊድሪ ስፖርት ኮሚሽን የአዲስአበባ ስታዲየምን ለማሳደስ እና ኢንተርናሽናል ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ከተቋራጭ ድርጅቱ ጋር ዛሬ የውል ስምምነት አድርጓል ።እድሳቱ በቅድሚያ ካፍ የሰጣቸውን አስተያየቶች መሠረት አድርጎ የሚሰራ ሲሆን የመጫወቻ ሜዳው ፣ የመልበሻና የመታጠቢያ ክፍሎች ፣ የተመልካች መፀዳጃ እና የኤሌክትሪክ እና የሳኒተሪ ስራዎችን ያካትታል ።
የእድሳቱን ስራውን ፍሬንድስ ኢንጅነሪንግ ኃ.የተ. የግል ኩባንያ በ39,644,748.93 ብር የአሸነፈ ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ እድሳቱን አጠናቆ ለማስረከብ በፊርማ ስነ ስርዓቱ ወቅት ገልጿል ።የኢፊድሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤሊያስ ሽኩር በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ እንደገለፁት ስታዲየሙ በቀጣይ ዓመት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድርን ጨምሮ በርካታ ኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን የሚያስተናግድ በመሆኑ እድሳቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥራቱን ጠብቆ ሊጠናቀቅ ይገባል ብለዋል ።
ኮሚሽኑም እድሳቱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል ።
የእድሳት ስራውን ዮሐንስ አባይ አርክቴክት ኢንጅነሪንግ አማካሪ ድርጅት የቁጥጥር እና የማማከር ስራ ይሰራል ።
የእድሳት ስራው በተሰራው ዲዛይን መሰረት የሚቀጥል ሲሆን በምዕራፍ ሁለት የሚዲያ ክፍሎች ፣ የክብር ቲሪቡን መቀመጫ ፣ የወንበር ገጠማ ፣እና ሌሎች የስታዲየሙ ክፍሎችን የማደስ እና ለአገልግሎት ምቹ የሚደረግ ይሆናል ።
@የኢፊድሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር