ዜናዎች

– በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ 51 የስፖርት ማዝወተሪያ ስፍራዎች ተጠናቀው ነገ ለምረቃ መዘጋጀታቸው ተገለፀ  !

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው በከተማው የስፖርት ማዝወተሪያ ስፍራዎች ልማትና ግንባታ በአመሪሩ ቁርጠኛ ክትትልና ድጋፍ እውን የሆኑ 51 የስፖርት ማዝወተሪያ ስፍራ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ነገ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ክብርት ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በተገኙበት በይፋ እንደሚመረቁ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር በላይ ደጀን አስታወቁ ።
ኮሚሽነር በላይ ደጀን  ለአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነት  ክፍል  በነበራቸው ቆይታ  እንደተናገሩት  ከ2013 ዓ.ም ወዲህ ባሉ ወራት አስተዳደሩ ለረዥም ጊዜ በነዋሪ ፣ በወጣቶችና በስፖርት ቤተሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችንና እሮሮዎችን በተጨባጭ አዳምጦ መሬት የወረደ መፍትሔ የሰጠባቸው የስፖርት ልማት ፕሮጀክቶች ነገ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ይሆናሉ ብለዋል ።
የስፖርት ልማትና ብልፅግናችንም በቀጣይም ይረጋገጣል ያሉት ኮሚሽነር በላይ ደጀን በተለይ ስፖርት ዋነኛ የልማትና የለውጥ አጋር መሆኑን በተጨባጭ የተረዱትና ውሳኔዎችን በቁርጠኝነት በመስጠትና በመከታተል 51 የስፖርት ማዝወተሪያ ስፍራዎች ግንባታ እውን እንዲሆን ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ በመመደብ ፣ የላቀ ሚናቸውን ከፊት ሆነው ለተወጡት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ለክብርት ወይዘሮ አዳነች አቤቤና አስተዳደራቸው ምስጋናቸውንና አክብሮታቸውን በከተማው ነዋሪ ፣ በወጣቶች ፣ በስፖርተኞች ፣ በስፖርት ቤተሰቡ ፣ በባለ ድርሻ አካላት እና በራሳቸው ስም አቅርበዋል ።
መንግስታችን ፕሮጀክትን ጀምሮ መጨረስ እንደሚችል ማሳያ የሆኑት የስፖርት ማዝወተሪያ ስፍራዎቻችን በነገው ዕለት በወጡ መርሀ ግብሮች የሚመረቁ ሲሆን መነሻ አራት ኪሎ ሲሆን የፈረንሳይ ጨፌ ሜዳ ፣ የአፍንጮ በር ሁለገብ የስፖርት ማዝወተሪያ እና የራስ ሀይሉ አለም አቀፍ ዘመናዊ የውሀ መዋኛ ገንዳ ግንባታዎች የምረቃው መዳረሻዎች መሆናቸው ታውቋል ።
ዘገባው እና ፎቶው የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነት ነው