ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ የእውቅና መርሀ ግብር ዛሬ መጋቢት 19/2013 ከቀኑ 10 : 00 ሰዓት ጀምሮ በስካይ ላይት ሆቴል ይካሄዳል።የእውቅናና የምስጋና መርሀ ግብሩን ምክንያት አስመልክቶ ከቀናት በፊት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተጠቆመው ጀግናዋ አትሌት በስፖርቱ አለም ላበረከተችው በርካታ ተግባራት አስተዋፅ እና እውቅና በመስጠት መጪውን ትውልድ ማነቃቃት መሆኑን የኮሚቴው አባል የሆኑት አትሌት ገዛህኝ አበራ የኢ.አ.ፌ ተቀዳሚ ምክ/ፕሬዝዳንት፣ አቶ ቢልልኝ መቆያ የኢ.አ.ፌ የጽ/ቤት ኃላፊ እና አቶ ነጋ ቱጁባ የኦሮሚያ አት/ፌዴሬሽን በጋራ በመግለጫው ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የባርሴሎና ኦሎምፒክ በ10 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ የመጀመሪያዋ አፍሪካዊቷ በመሆን በሴቶችም የክቡር ሻለቃ አትሌት ኃይሌገ/ስላሴን የ‹‹ይቻላል›› መንፈስ እንዲተገበር ተጠቃሽ መሆኗ ተገልጿል። በዚህ ፕሮግራም ላይ 20 ሚኒስተሮች የክልል ከንቲባዎችና ፕሬዝዳንቶች፣ የፌዴራልና የክልል ስፖርት ኮምሽን አመራሮች፣ የክልል አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሃላፊዎች ፣ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች እና በኦሎምፒክ ኢትዮዽያን ያስጠሩ አትሌቶች ጥሪ ተደርጎላቸዋል።ከዚህ በተጨማሪም ፕሮግራሙ ከስካይ ላይት ሆቴል በቀጥታ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እና በOBN የሚተላለፍ መሆኑ ተጠቁሟል።
ለኮማንደር ደራርቱ ቱሉ እውቅና ከሚሰጥባቸው ተግባራት መካከል :-
– በኦሎምፒክ በ10ሺህ ሜትር የመጀመሪያዋ ጥቁር አፍሪኳዊት የወርቅ ሜዳሊስት በመሆኗ
-በተለያዩ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የአትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ላይ በስመዘገበችው በርካታ ውጤቶች
– ከስፖርቱ ጎን ለጎን በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ተሰማርታ በሆቴል እና ቱሪዝም ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የሥራ እድል መፍጠር በመቻሏ
– በአትሌቲክሱ ዘርፍ ውጤታማ አትሌት ከሆነችም በኃላም ከሙያው ባለመራቅ በፌዴሬሽኑ ውስጥ ከተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንትነት እስከ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንትነት እየሰራች መሆኗ
– በተጨማሪም የምስራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ሪጅንን በምክትል ፕሬዝዳንትነት እየሰራች ትገኛለች
– ከዚሁ ጎን የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን የካውንስል አባል በመሆን እያገለገለች መገኘቷ በዛሬው የእውቅና ፕሮግራም ላይ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል።