ዋልያዎቹ በአስደናቂ የድል ዜማ ለአፍሪካ ዋንጫ ተቃርበዋል !
በካሜሩን አዘጋጅነት ለሚካሄደው ቀጣይ የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የማዳጋስካር አቻውን በ 4 ለ 0 ድል አሸንፎ ወጥቷል። የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድን ተጋጣሚውን በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በሰፊ የጎል ልዩነት ማሸነፍ ከመቻሉ በተጨማሪ በጨዋታው ብልጫም አሳይቷል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የጨዋታውን የመጀመሪያ ጎል በ19ኛው ደቂቃ በአማኑኤል ገ/ሚካኤል አማካኝነት አስቆጥሮ የማጥቃት የበላይነቱን አጠናክሯል።
በጨዋታው የበላይነት የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአምበሉ በጌታነህ ከበደ አማካኝነት በ34ኛው ደቂቃ ያገኘውን የቅጣት ምት ወደ ጎል በመመንዘር ጨዋታውን ዋልያዎቹ በበላይነት እንዲቀጥሉ አስችሏል። የመጀመሪያው አጋማሽ ከመጠናቀቁም በፊት በማጥቃት ሂደት ላይ እተጫወተ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግን በ21 ጎሎች በተቆናጠጠው አቡበከር ናስር ሶስተኛውን ጎል በ41ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል። ለጎሏ መገኘት የሱራፌል ዳኛነው ሚና ከፍተኛ ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽ በ3 ለ0 የኢትዮጵያ የበላይነትን ከተጨናቀቀ በኃላ በሁለተኛው አጋማሽ ማዳጋስካሮች ውጤቱን መለወጥ የተጨዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በማዳጋስካር በኩል የባህርዳር ሞቃታማ አየር የከበዳቸውም ሆኖ ታይቷል። የሁለተኛው አጋምሽ የጨዋታ አንቅስቄሴ ዋልያዎቹ በማጥቃትና በመከላከል የተሻሉ ሆነው ታይተዋል። በማዳጋስካር በኩል ከ75 ደቂቃ በኃላ የአጥቂው ክፍል ለውጥ መደረጉ ጎል ለማስቆጠር ተደጋጋሚ ሙከራዎች ቢያደርጉም ሙከራው ሳይሳካ ቀርቷል።
በጨዋታው መጠናቀቂያ አካባቢ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምክትል አምበሉ በሽመልስ በቀለ አማካኝነት አራተኛውን ጎል አስቆጥሮ የአፍሪካ ዋንጫን ከስምንት አመት በኃላ ዳግም ለመቀላቀል መንገዱን ያመቻቸ ውጤት ይዞ ወጥቷል። በዛሬው የውጤት መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ9 ነጥብ ምድቡን ይመራል። በኢትዮጵያ ምድብ የሚገኙት ከአይቮሪኮስት ከኒጀር የፊታችን አርብ ምሽት የምድቡን ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ የመጨረሻ ጨዋታን ከስድስት ቀናት በኃላ ከአይቮሪኮስት ጋር ወደ አቢጃን ተጉዞ ያደርጋል።
የጨዋታውን ሁሉንም ጎሎች እዚህ ቪዲዮ ላይ ይመልከቱ።
ጥሩ ነዉ በርቱ