አፍሪካ ዜናዎች

ፊፋ በወልቂጤ ከተማ ግብ ጠባቂ ሲልቫይን ግቦሆ ላይ የዕገዳ ውሳኔ አሳልፏል !

የፊፋ ዲሲፕሊን ኮሚቴ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በላከው መልዕክት ሲልቫይን ግቦሆን በጊዜያዊነት እንዳገደ አስታውቋል።ለአይቮሪኮስት ብሔራዊ ቡድን እየተጫወተ የሚገኘው ሲልቫይን ግቦሆ በአሁኑ ወቅት በወልቂጤ ከተማ ተመዝግቦ እየተጫወተ የሚገኝ ሲሆን ኖቬምበር ላይ አይቮሪኮስት ከጋቦን ጋር ስትጫወት በእጣ የዶፒንግ ምርመራ እንዲሰራለት ወጥቶበት የሽንት ናሙና ሰጥቶ ነበር። በዚህ ናሙና ውስጥም ትራይሜታዚዲን የሚባል ከ2014 ጀምሮ አትሌቶች እንዳይጠቀሙት በዋዳ የታገደ ንጥረ ነገር ተገኝቷል።

 
ንጥረ-ነገሩ በደም ስር መጥበብ ምክንያት የሚመጣ የልብ በሽታዎችን ለማከም የሚጠቅሙ መድሃኒቶች ላይ የሚገኝ ሲሆን የልብ ጡንቻዎችን የግሉኮስ አጠቃቀም ያጎለብታል። በዚህ ምክንያትም በዓለም አቀፉ ፀረ-አበረታች መድሃኒት እና ቅመሞች ቁጥጥር ኤጀንሲ ጥቅም ላይ እንዳይውል ተከልክሏል። ለህክምናው ሌላ አማራጭ በማይኖርበት ጊዜ ይህንን በሐኪሞች በማረጋገጥ ‘ልዩ ለህክምና የመጠቀም ፈቃድ’ ወይም ‘Therapeutic Use Exemption’ (TUE) ከWADA በማግኘት መጠቀም የሚቻል ቢሆንም ሲልቫይን ግን ይህ ፈቃድ እንደሌለው ኤጀንሲው አስታውቋል። በህጉ መሰረትም ይህ ሲያጋጥም ወዲያው ጊዜያዊ ዕገዳ በተጫዋቹ ላይ ከተጣለ በኋላ በዲሲፕሊን ኮሚቴው የመጨረሻ ውሳኔ ከአጭር ጊዜ በኋላ የሚሰጥ ይሆናል።
 
በዚህም መሰረት የፊፋ ዲሲፕሊን ኮሚቴ ተከታዩን ውሳኔ በተጫዋቹ ላይ አሳልፏል፦
 
1- ይህ ውሳኔ ከተገለጸበት ቀን ጀምሮ ሲልቫይን ግቦሆ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጊዜያዊነት ይታገዳል።
 
2- ይህ ጊዜያዊ እገዳ ሀገር አቀፍ ወይም ዓለም አቀፍ ውድድር ያካተተ ነው።
 
3- በፊፋ የፀረ-አበረታች መድሃኒት ህግ (2021 ed.) ውስጥ በተካተቱት ድንጋጌዎች መሰረት ቀደም ብሎ ካልተቋረጠ በስተቀር ጊዜያዊ እገዳው በፊፋ የዲሲፕሊን ኮሚሽን የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጥበታል።
 
@EFF