የስፖርት ትጥቅ ብራንድ ጎፈሬ ከሀገር አልፎ በመላው ዓለም ምርቶቹን ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ ይታወቃል። ጎፈሬ በአጋርነት ከሀገር ውጪ አብሯቸው ከሚሰራቸው ታላላቅ ተቋማት መካከል በሀገረ አሜሪካ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያሳትፈው ግራንድ አፍሪካ ረን እንዲሁም ለሀገራቸው ታላላቅ ገድሎችን ለፈፀሙ የሀገር ባለውለታዎች እውቅና የሚሰጠው ኢምፓክት አዋርድ ዝግጅቶችን ከሚያዘጋጀው ኖቫ ኮኔክሽንስ ጋር ያለፉትን ሁለት ተከታታይ ዓመታት የሰራ ሲሆን አሁንም ከተቋሙ ጋር ያለውን ውል አራዝሟል።
ዛሬ ከሰዓት በውቡ የጎፈሬ ሾ ሩም በተከናወነው ጋዜጣዊ መግለጫ የጎፈሬ መስራች እና ባለቤት አቶ ሳሙኤል መኮንን እንዲሁም የኖቫ ኮኔክሽንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ጋሻው አብዛ በርካታ ሚዲያዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የጎፈሬ ብራንድ አምባሳደሮች ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ እና አልቢትር ባምላክ ተሰማ በተገኙበት የፊርማ ሥነ-ስርዓት አከናውነዋል።
ለቀጣዮቹ 3 ዓመታት በተራዘመው የውል ስምምነት በዋሺንግተን ዲሲ ኖቫ ኮኔክሽንስ በሚዘጋጃቸው ሁለቱም ታላላቅ ዝግጅቶች ጎፈሬ ብቸኛ የስፖርት ትጥቅ አጋር ሲሆን በአንደኛ ደረጃ ካሉ የዝግጅቶቹ ታላላቅ አጋሮች መካከልም እንደሚቀመጥ ተገልጿል።
በመግለጫው ዶክተር ጋሻው አብዛ በሀገረ አሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና የሌሎች ሀገር ዜጎች “ይህ እጅግ ጥራት ያለው ምርት ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ ጥራት ልክ ይመረታል?” ብለው እንዳልጠበቁ ጠቁመው ውሉ በመራዘሙ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል። የጎፈሬ ባለቤት አቶ ሳሙኤል በበኩላቸው ምህዳሩን እያሰፋ የሚገኘው ድርጅታቸው በቀጣይም በሀገረ አሜሪካ ተመራጭ የሆነውን ብራንድ ከዚህ የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ አመላክተው በውሉ መሰረት በቀጣዮቹ ዓመታት በብዛትም በጥራትም አዳዲስ ምርቶችን ተደራሽ እንደሚያደርጉ አስረድተዋል።
ጎፈሬን ወክለው በ6ኛው ግራንድ አፍሪካ ረን እና ኢምፓክት አዋርድ የተገኙት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በበኩላቸው ባሳለፍነው ጥቅምት ወር ተገኝተው ስለታዘቡት ነገር ሲናገሩ በቅዳሜው የ5 ኪ.ሜ ሩጫ በርካታ ኢትዮጵያውን በጋራ ሀገራቸውን አስቀድመው በቤተሰብ መንፈስ ፕሮግራሙን እንደሚያካሂዱ እንዲሁም እሁድ ቀን የሚደረገው ኢምፓክት አዋርድ ላይ ከሀገር አልፎ ለአፍሪካ እና ለዓለም አስተዋጽኦ ያደረጉ ባለውለታዎች በሚገባቸው ልክ ዕውቅና ሲሰጣቸው እንደተመለከቱ ተናግረዋል።
ከማብራሪያው በኋላ የፊርማ ስምምነቱ ተከናውኖ የ2025 የመሮጫ ቲ-ሸርት ይፋ ሆኗል።
በምርቶቹ ጥራት የዋሺንግተን ዲሲ ከንቲባ እንዲሁም በሜሪላንድ ግዛት የሞንቶጎሞሪ ካውንቲ አስተዳደር ለጎፈሬ የዕውቅና ሰርተፊኬት መስጠታቸው ይታወሳል።