የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አልጣኝ ውበቱ አባተ እና አምበሉ ጌታነህ ከበደ ነገ ምሽት 4፡00 ላይ ኢትዮጵያ ከኬፕ ቨርድ ከምታደርገው ጨዋታ ቀደም ብሎ ዛሬ በተዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሀሳባቸውን በስፍራው ለተገኙ ጋዜጠኞች አካፍለዋል።
ወደ ካሜሩን ለመድረስ የመጀመርያው ቡድን እንደሆንን በመግለፅ መግለጫቸውን የጀመሩት አሰልጣኝ ውበቱ ከሶስት አፍሪካ ዋንጫዎች በኋላ ወደ መድረኩ በመመለስ ጥሩ ቡድን ይዘው ለመቅረብ እና ማንነታቸውን ለማሳየት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል። ከስምንት ዓመት በኋላ ወደ ውድድሩ እንደመመለሳቸው አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ዘንድሮ ለሚተገበረው ቪኤአር ቴክኖሎጂ አዲስ ቢሆኑም ያን ያህል ልዩነት እንደማይፈጥርም ተናግረዋል። ” አብዛኛዎቹ ተጫዋቾቻችን በሀገራችን ሊግ የሚጫወቱ በመሆናቸው ይህ ለኛ አዲስ ተሞክሮ ነው። ነገር ግን ቡድኖች ውጤት ማግኘት ያለባቸው በሜዳ ላይ በሚያሳዩት ነገር ነው። ስለዚህ እኛ በዚህ ጉዳይ ላይ ችግር የለብንም። ” ብለዋል።
በዘንድሮው ውድድር ላይ ዝቅተኛ ግምት እንደተሰጣቸው ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው አሰልጣኝ ውበቱ ” ሁሉም ሰው ለኛ አነስተኛ ግምት ነው የሰጠን። የፊፋ ደረጃ ላይ ያለን ቦታ ዝቅተኛ ነው። ደረጃው ግን ያለንበትን ሁኔታ አመላካች ነው ለማለት ይከብዳል። ሁላችንም እንደምናውቀው ተጋጣሚዎቻችን ጠንካሮች እና በጥሩ ተጫዋቾች የተዋቀሩ ናቸው። ሆኖም እኛም ለመፎካከር እና ያለንን ነገር ለማሳየት ተዘጋጅተናል። ማንም ባይጠብቀንም ጥሩ ነገር ለማሳየት ዝግጁ ነን። በማጣርያው ላይ ቡድናችንን ተመልክታችሁታል። እንደከዚህ ቀደሙ አይነት ቡድን አይደለም ያለን። ” ሲሉ ተደምጠዋል።
መግለጫው ቀጥሎ ስለአዘጋጇ ካሜሩን የተጠየቁት አሰልጣኝ ውበቱ ጉዳዩን በሁለት መልኩ መመልከትን መርጠዋል። ” ይህን በጥሩም ሆነ ጥሩ ባልሆነ ጎኑ መመልከት እፈልጋለሁ። ካሜሩን ጠንካራ ቡድን መሆኑን እና በሀገሩ እና በደጋፊው ፊት እንደሚጫወት እናውቃለን። ይህ ለእነሱ ጠቃሚ ነው። በሌላ ጎኑ ስናየው ደሞ ለነሱ ጫና የሚፈጥር እና እኛን ከጫና ነፃ እንድንሆን የሚያደርግ በመሆኑ ለኛ ጠቃሚ ነው።” ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ የውድድሩ አሸናፊ እንደነበረች ያወሱት አሰልጣኙ በዚህ ውድድር ላይ የመጀመርያ እቅዳቸው ከምድብ ማለፍ እንደሆነ ተናግረው ለመካፈል ብቻ ካሜሩን እንዳልተገኙ ”ለህጉራችን እና ለዓለም ምን እንዳለን ለማሳየት ተዘጋጅተናል። በርካታ አቅም ያላቸው ተጫዋቾች አሉን። ይህን ለእግርኳሱ ዓለም ማስተዋወቅ አለብን። በሌላ በኩል ሌሎቹ ቡድኖች ልምድ አላቸው። ግን የተለየ ነገር ለማሳየት እና ሰርፕራይዝ ቡድን ለመሆን ተዘጋጅተናል። ‘ በማለት አላማቸውን ገልፀዋል።
ነገ አራት ሰአት ላይ የመድረኩ የምድብ ጨዋታዋን ኬፕ ቨርድን በመግጠም የምትጀመረው ኢትዮጵያ ከጨዋታው ምን እንደምትጠብቅ ለአሰልጣኝ ውበቱ ጥያቄ ቀርቦላቸው ” የነገው የመጀመርያ ጨዋታ ነው። ስለዚህ ሁለቱም ቡድኖች እኩል እድል አላቸው። እነሱ ጠንካሮች ቢሆኑም እኛም የተሻለ ነገር ለማሳየት ዝግጁ ነን። ምድቡን በተመለከተ ቡድኖቹ ጠንካራ ናቸው፤ እናከብራቸዋለን። የተለየ ክብደት የምንሰጠው ቡድን ግን አይኖርም። ይህ እግር ኳስ ነው። ” ብለዋል።
የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ስለ ዝግጅታቸው እና የካሜሩን ቆይታቸው ሀሳባቸውን መስጠት ቀጥለው ” ሳኡዲ አረቢያ ነበር ሀሳባችን ፤ ግን በነበረው የጉዞ ክልከላ ምክንያት ወደ ካሜሩን መጥተናል። እኛ ከመምጣታችን በፊት ብዙዎች የአፍሪካ ዋንጫ ላይካሄድ ይችላል የሚል ጥርጣሬ ነበራቸው። እኛ ካሜሩን በቅድሚያ መድረሳችን ግን ውድድሩ እንደሚካሄድ አመላካች ሆነናል። ከዚህ ባሻገር እዚህ ቶሎ በመምጣታችን ተጠቅመናል። የወዳጅነት ጨዋታ ማድረግ እንድንችል እንዲሁም ሁላችንም በአንድ ቦታ ተሰባስበን ከኮቪድ እና መሰል ችግሮች እንድንርቅ አድርጎናል። ”
” እዚህ እንደመጣን በኮቪድ ተቸግረን ነበር። አምስት እና ስድስት የሚሆኑ ተጫዋቾች ለቀናት ልምምድ መሥራት አልቻሉም ነበር። አሁን ላይ ሁሉም ተጫዋቾች ነፃ መሆናቸው ለእኛ መልካም ዜና ነው። በጉዳት ረገድ ሽመልስ በቀለ እና ዳዋ ሆቴሳ በሀርምስተሪንግ እና የቁርጭምጭሚት ጉዳት ለነገው ጨዋታ መድረሳቸው አጠራጣሪ ከመሆኑ በቀር ሌሎቹ በጥሩ ጤንነት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።
ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር አብሮ መግለጫው ላይ የተገኘው አምበሉ ጌነህ ከበደ ለሁለተኛ ጊዜ በመድረኩ ላይ ተሳትፎ እንደሚያደርግ ገልፆ የነገውን ጨዋታ በጥሩ ሁኔታ ለማከናወን እንደተዘጋጁ ተናግሯል። በጨዋታዎች ላይ የቪኤአር መኖርም ለቡድናችን ጥሩ እንደሆነ ሀሳቡን ሰጥቷል። ” በማጣርያው ከነ ጋና ጋር ከመጫወታችን በፊት በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ከአይቮሪኮስት ጋር ጥሩ ነገር አሳይተናል። የተሻልን ነበርን። ውጤቱ ባይገልፀውም ጥሩ ተንቀሳቅሰን ነበር።” ሲልም ቡድናቸው ጠንካራ እንደሆነ ተናግሯል።
ብሔራዊ ቡድናችን ዛሬ ምሽት ላይ ከነገው ጨዋታ አስቀድሞ የመጨረሻ ልምምዱን ያከናውናል።