ዜናዎች

” የመጨረሻው ዕድላችንን ይሄ ብቻ ስለሆነ ያለንን ነገር ለጅማአባጅፋር ለመስጠት ዝግጁ ነን ” ወንድማገኝ ማርቆስ(ቾንቤ)

ወንድማገኝ (ቾንቤ) ከቡድን አጋሮቹ ጋር
የጅማ አባጅፋሩ የቀኝ መሥመር ተጨዋች ወንድማገኝ ማርቆስ(ቾንቤ) በክለቡ ደጋፊዎች ተወዳጅ  ከሆኑ ተጨዋቾች አንዱ ነው። የወንድማገኝ ቡድን ጅማ አባጅፋር በ2013 የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ያጠናቀቀው በደረጃ ግርጌ ውስጥ ከሆኑ ሶስቱ ከወራጅ ክለቦች አንዱ ሆኖ ነው።
በአንፃሩ የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የ2014 የፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦችን በተመለከተ ባስተላለፈው የ2ኛ አማራጭ ውሳኔ የትግራይ ክልል ሶስቱ ክለቦች ባለመሳተፋቸው የወንድማገኝ እና ጅማ አባጅፋር ነገ በሚጀመረው የጥሎማለፍ ውድድር ወደ ሊጉ ለመመለስ ታላቅ ተስፋ ይዘዋል።
የጅማ አባጅፋር ወንድማገኝ ማርቆስ(ቾንቤ) ዳግም ወደ ሊጉ ለመመለሥ ከፍተኛ አቅም ላይ ነን ሲል ከኢትዮ ኪክ በነበረው ቆይታ ይናገራል። 
ኢትዮ ኪክ :- የዘንድሮው ቤትኪንግ እንዴት ነበር ቆይታችሁ ?
ወንድማገኝ :- የዘንድሮ ቤትኪንግ ጥሩ ነው ደስ ይላል..ለተጨዋቾች በጣም አሪፍ ነው ።
ኢትዮ ኪክ :- ለዝግጅት ሐዋሳ ነበራችሁ ሰሞኑን አሁንም ?
ወንድማገኝ :- አዎ ሀዋሳ ነን። አንድ ሳምንት አልፎናል ዝግጅት ከገባን
ኢትዮ ኪክ :- እንዴት ነው ቤትኪንግ ለመመለስ ለሚደረግ የተለየ ዝግጅት አለ ?
ወንድማገኝ :- ዝግጅት በጣም በጥሩ ሞራል እና ተነሳሽነት የሰራን ነው
ኢትዮ ኪክ :- ዘንድሮ ቤትኪንግ ጨዋታዎች በወጥ አቋም መቀጠል ያልቻላችሁት በአንተ እይታ ምን ነበረ ?
ወንድማገኝ :- በመጀመሪያ አጀማመራችን ጥሩ አልነበረም። ከዛም በኃላ መሻሻል ነበር። ከመጀመሪያ ያጣነው ነገር መጨረሻችንን አበላሸብን ነው የምለው።
ኢትዮ ኪክ :- ምናልባት ለእዛ እንደ ዋና ችግር የሚቀመጥ ነገር ይኖራል?
ወንድማገኝ :- እንደዋና ምለው ነገር መጀመሪያ የደሞዝ ችግር ነበር እሱ ቀስ በቀስ እየተቀረፈ መጥቷዋል..
ኢትዮ ኪክ :- ከደሞዝ ጋር የሆቴልና የምግብ እንዲሁም ስትዘዋወሩም በጣም ችግር ላይ ነበራችሁና በግልጽ ተፅኖ አድርጓል ማለት ይቻላል ?:
ወንድማገኝ :- አዎ እንደዛም የሆነ ችግር ነበር ልክ ነው። አሁን ላይ ከአንዳንድ ቦታ ገንዘብ የገባ ስለሆነ እሱ ነገር ይደገማል ብዬ አላስብም።
ኢትዮ ኪክ :- አሁን የስንት ወሩ ደሞዝ ተቀርፏል ?
ወንድማገኝ :- ደሞዝ የአንዳንድ ልጆች የዚህ ወር አላቸው የተወሰኑ ልጆች ደሞ የሁለት ወር አላቸው።
ኢትዮ ኪክ :-ስለዚህ አሁን ሐዋሳ ቤትኪንግ ለመመለስ ታላቅ የፍልሚያ ዝግጅት ናችሁ ማለት ይቻላል ?
ወንድማገኝ :- እንዴ በትክክል ምን ጥያቄ አለው። አሪፍ እኮ አንዴ ነው ሚሸወደው የሚባል ነገር አለ.. የመጨረሻ ዕድላችን ይሄ ብቻ ስለሆነ ያለንን ነገር ለጅማአባጅፋር ለመስጠት ዝግጁ ነን።
ኢትዮ ኪክ :- ምን የተለየ ነገር ይዛችሁ ነው የምትመጡት በአጭር ጊዜ ዝግጅት ?
ወንድማገኝ :- እግርኳስ የሚፈቅደውን ነገር ሁሉ እናደርጋለን ሁሉንም ጨዋታ እንደ ፋይናል አስበን ነው የምንጫወተው።
ኢትዮ ኪክ :- ከቲሙ ጋር ኮንትራትህ መቼ ያልቃል ?
ወንድማገኝ :- ዘንድሮ ጨርሳለው
ኢትዮ ኪክ :- ስለዚህ ምን አስበሃል?
ወንድማገኝ :-እንደማንኛውም እግር ኳስ ተጫዋች የተሻለ ቦታ መጫወት እፈልጋለሁ
ኢትዮ ኪክ :- በዘንድሮው ውድድር በግልህ ኮከብ ተጨዋች የምትለው ?
ወንድማገኝ :- ዘንድሮ የተለየ ተጫዋች ለእኔ አቡኪ ነው። ምንም ጥያቄ የለውም ..ግን ሁለት ንጉስ አይኖርም እንጂ ለያሬድ ባዬ የተለየ ክብር አለኝ ።
ኢትዮ ኪክ :- ስለዚህ በቀጣይ ዓመት ጅማአባጅፋር በቤትኪንግ ይኖራል ብለህ መናገር ትደፍራለህ ?
ወንድማገኝ :- በደንብ እንጂ። ምንም የምጠራጠረው ነገር የለም ። ባገኘነው ዕድል ተጠቅመን ቀጣይ አመት ቤትኪንግ ዘላቂ ነን።
ኢትዮ ኪክ :- አመሠግናለሁ ስለ ምላሽህ
ወንድማገኝ :- እኔም አመሠግናለሁ