ቤትኪንግ ፕሪሜር ሊግ ዜናዎች

“ክለባችንን ለኮንፌዴሬሽን ማሳለፍ እና ራሴም ሪከርዱን መስበር ነው የምፈልገው ፤ እናሳካለን ብዬ አስባለሁ” ➖አቡበከር ናስር

የኢትዮዽያ ቡናው አቡበከር ናስር በሊጉ በዘንድሮው የውድድር ዓመት በክለቡ ከተቆጠሩ 38 ጎሎች 24ቱን ያስቆጠረ ሲሆን በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጌታነህ ከበደ በ 30 ጨዋታዎች  የተያዘውን   የ25 ጎሎች ሪከርድ ለመስበር የመጨረሻው ምህራፍ ላይ ይገኛል። አቡበከር ናስር በዛሬው ጨዋታ የሊጉን 24ኛ ጎል በማስቆጠር በኢትዮጵያ ቡና ክለብ 10 ቁጥር ማሊያ የጎል አዳኝ ከነበረውን ከታፈሰ ተስፋዬ  ሪከርዱን ተረክቧል ።  ታፈሰ በ2001 የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ሲያጠናቅቅ በተሰለፈበት 26 ጨዋታዎች  ያስቆጠረው 23 ጎልነበር ። አቡበከር ናስር በኢትዬጵያ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ ከፍተኛ ጎል ያስቆጠረ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋች  ሲሆን  በ  23 ጨዋታዎች 24  ጎሎች  ያስቆጠረ  ሆናል  ። በ1993 ዮርዳኖስ አባይ በኤልፓ እያለ  በ 32 ጨዋታዎች   ካስቆጠረው የ24ጎሎች ሪከርድ ጋር ተተስተካክሎ ዋናውን የሊጉን ሪከርድ ለመስበር ቀሪዎቹን ሶስት ጨዋታዎች ይጠብቃል። ከዚህ በተጨማሪም አቡበከር ናስር በዛሬው ዕለት በሊጉ ከሀያ ሶስት ጎሎች በላይ ያስቆጠረ አምስተኛው ተጫዋች መሆንም ችሏል። ከጨዋታው በኋላ አቡበከር ናስር ከሱፐር ስፓርት ጋዜጠኛ ሰኢድ ኪያር ጋር ቆይታ አድርጓል።
በቅድሚያ እንኳን ለዒድ አልፈጥር በዓል አደረሰህ
” እንኳን አብሮ አደረሰን “
ዛሬ ሁለት ጎሎች አስቆጥረሃል ጨዋታው ኦንዴት ነበረ?
” ጨዋታው ከባድ ነበር ። ምክንያቱም እኛ አሁን እድላችን ለሁለተኛነት ስለሆነ። ከኃላም ያሉት ቡድኖች እና ከባህርዳር ጋር የተጫወትነው አንድ ነጥብ ላይ። እነሱን መራቅ ነበር የምንፈልገው እነሱም በጥንቃቄ ነበር ሲጫወቱ የነበሩት ። እኛም በጥንቃቄ ነበር ስንጫወት የነበረው። ያው አላህ  አላለውም ፣ ማሸነፋችን አልቻልንም ። ያው ለቀጣይ ግን ራሳችንን አዘጋጅተን እንመጣለን”
ባለፉት ጨዋታዎች ጎል ያለማስቆጠሩ እና ጎል ሳላስቆጥር ወደ ሪከርዱም ሳልመጣ የሚል ስሜት ተሰምቶት እንደነበረ?
” በፍጹም አልተሰማኝም። ምክንያቱም እኔ በመጀመሪያ ክለባችንን  ለአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ማሳለፍ የምፈልገው፤ ከጓደኞቼ ጋር ሆኜ ፣ ግን እንደዛም ሆኖ እሱንም አሳክቼ ራሴም ሪከርዱን መስበር ነው የምፈልገው፣ ቀጣይ ጨዋታዎች ራሳችንን በጥንቃቄ ተጫውተን ለአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን እና ሪከርዱንም እናሳካለን ብዬ አስባለሁ”
ዛሬ ባስቆጠረው ሁለት ጎሎች ከዮርዳኖስ አባይ ጋር እኩል መሆኑ የሚፈጥርበት ስሜት ?
” አዎ ። ምክንያቱም ዮርዳኖስ አባይ ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ ከሚባሉ ትልቅ አጥቂዎች ተርታ አንደኛውና ያው እሱ ሲጫወት አላጋጠመኝም ግን በምሰማው ነገር እና አንዳንድ ቪዲዮችን በማየት ደግሞ  ትልቅ ተጨዋች ነው። የእሱን ሪከርድ በመጋራቴ እንዲሁም ደውሎ አበረታቶኛልና ማመስገን እሱን እፈልጋለሁ “
ከዚህ በኃለ ባሉት ጨዋታ ስለሚያስበው ?
” ኢህሽ አላህ  ፣ ከአላህ ጋር ሆኜ በሚቀጥለውም ጨዋታ እራሴን አዘጋጅቼ ለመምጣት ነው የምፈልገው። ከጓደኞቼ ጋር ሆኜ ውጤቱም ያስፈልገናልና ። ቀጣይ ጨዋታ ደግሞ ከሲዳማ ቡና ጋር ነው ፣ በጣም ከባድ ነው። ራሳችንን ለሁለተኝነት ጠንክረን እንሰራለን፣ ያሉብንን ክፍተቶች ሞልተን ሁሉም ከበረኛው እስከ አጥቂው ሁሉም ራሳችንን አዘጋጅተን እንቀርባለን ብዬ አስባለሁ”
ሁለቱ ጎሎች ለማን ይሁኑ
” ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች አንኳን አደረሳችሁ ማለት እፈልጋለሁ። ይህም ሁለት ጎሎች ለመላው የእስልምና እምነት እና ለኢትዮጵያ ስፓርት አፍቃሪዎች ማመስገን እፈልጋለሁ ፣ ለእነሱ ይሁንልኝ”