ዜናዎች

ካፍ ያስተላለፈው ውሳኔ ወቅቱን ያልጠበቀ እና እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ግምት ውስጥ ያላስገባ መሆኑ ተገለፀ !

 
የባህርዳር ስታድየም በካፍ ልዑክ ተገምግሞ በቀጣይ ኢንተርናሽናል ጨዋታወችን እንዳያስተናግድ እገዳ መጣሉ ይታወሳል።የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የተላለፈው ውሳኔ ወቅቱን ያላገናዘበና እየተሰሩ ያሉ ስራወችን ግምት ውስጥ ያላስገባ መሆኑን ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ አስታውቋል ።
በመግለጫው ካፍ ለእገዳው በምክንያትነት ካነሳቸው አስተያየቶች መካከል የተጨዋቾች መልበሻ ክፍል ግብዓቶችን ማሟላት፣የVIP ጣራ ስራ፣ የሚድያ ክፍል ማዘጋጀት፣ የተጠባባቂ ተጨዋቾች መቀመጫ፣እንዲሁም የሜዳ ሳር እንዲቀየር የሰጠው አስተያየት አግባብነት የሌላቸው አስተያየቶች ናቸው ሲሉ በክልሉ የስፖርት ፋሲሊቲ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ባንታምላክ ሙላት ገልፀዋል።
ዳይሬክተሩ ጨምረው እንደገለፁት ሌሎች አስተያየቶች ማለትም ስታድየሙን ጣራ ማልበስ፣ በምሽት ጨዋታወችን ማካሄድ የሚያስችል የመብራት(flood light) ስራ፣የተመልካቾች መቀመጫ ወንበር እና የስርዓተ ድምፅ ግብዓቶችን ማሟላት ከፍተኛ ወጭ የሚጠይቁና ከክልሉ መንግስት አቅም በላይ በመሆናቸው በክልሉ መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አማካኝነት ከሚመለከተው አካል ጋር መነጋገር ተጀምሯል ብለዋል ።
የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ም/ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ ካሳ በበኩላቸው የባህርዳር አለም አቀፍ ስታድየም ለበርካታ አመታት የተለያዩ ኢንተርናሽናል ጨዋታወችን በማስተናገድ ለአገር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከተ በመሆኑ ፋይዳው አገራዊ መሆኑን ጠቁመው ፤ ስታዲየሙ ስታንዳርዱን እንዲያሟላ ካፍ ከሰጣቸው አስተያየቶች መካከል በክልሉ አቅም ሊሸፈኑ የሚችሉትን ለመስራት የአጭር፣ መካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅድ ተዘጋጅቷል ብለዋል።
በቀጣይም ስታድየሙ የሚያስፈልጉትን ግብአቶች በማሟላት አለም አቀፍ ደረጃውን አሟልቶ ወደ ውድድር አንዲመለስ የሁሉም አካላትን ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑ ታውቆ ሁሉም አካል የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
መረጃው የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ነው