በካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመሰለፍ ከፍተኛ ፍላጎታቸውን የስካውቲንግ ስራውን ፌዴራሽኑ ኃላፊነት በሰጠው በዴቪድ በሻህ በኩል ገልፀው የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የመጨረሻ ምላሽ ምን እየተጠበቀ ነው።
እኛም በቅርቡ በሚጀምረው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ ዴቪድ በሻህ ስም ዝርዝራቸውን ይፋ የሆኑትን ተጨዋቾችን በማነጋገር እና የተለያዮ መረጃዎችን ከስካውቲንግ ስራውን ከሚሰራው ዴቪድ በሻህ ጋር በቀጣይ ቀናት ለእናንተ የምናቀርብ ይሆናል ።
ለዛሬው ግን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመጫወት የፌዴሬሽኑን በር በተዳጋጋሚ አንኳኩቶ ምልሽ የተነፈገው እና ከኢትዮጵያዊ አባት እና ከስፔናዊ እናቱ በጀርመን ከትውልደው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ኬኒ ፕሪንስ ሬዶንዶ ጋር ኢትዮ ኪክ ቀለል ያሉ አዝናኝ ጥያቄዎችን አቅርበን ምላሹ ሰጥቶናል።
የ27 ዓመቱ ኬኒ ፕሪንስ ሬዶንዶ የአንድ ልጅ አባት ሲሆን በጀርመን የተለያዬ ፕሮፌሽናል ሊጎች የተጫወተ እና አሁን በጀርመን የ 3ኛ ዲቪዚዮን ካይዘርስላውተር በሁለቱም በኩል የክንፍ እየተጨወተ ይገኛል። ኬኒ ፕሪንስ በ2020 የፈረንጆቹ የበጋ የዝውውር ወራት ከሁለተኛ ዲቪዚዮኑ ለSpVgg Greuther Fürth ወደ ሌላኛው የጀርመን ክለብ ሶስተኛ ዲቪዚዮን ካይዘርስላውተር ከተቀላቀለ በኃላ ከአዲሱ ክለቡ ጎሎችን በተደጋጋሚ እያስቆጠረም ይገኛል።
ከትውልደ ኢትዮጵያዊው ኬኒ ፕሪንስ ሬዶንዶ ጋር ኢትዮ ኪክ ያደረግነው አዝናኝ ጥያቄዎች
ኢትዮኪክ :- ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የመጫወት ዕድል ብታገኝ እና በአፍሪካ ዋንጫ ጎል ብታስቆጥር የጎሏን መታሰቢያ ለማን ታደርጋለህ ?
ኬኒ ፕሪንስ :- ለአባቴ እሰጥ ነበር።
ኢትዮኪክ :- በብሔራዊ ቡድን ደረጃ እድል ብታገኝ ለየትኛው መጫወቱን ትመርጣለህ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወይስ ለጀርመን ብሄራዊ ቡድን ?
ኬኒ ፕሪንስ :- ከጀርመን ይልቅ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መጫወትን እመርጣለሁ።
ኢትዮኪክ :- በጀርመን ሊጎች ስትጫወት ከዘረኝነት ጋር በተያያዘ መጥፎ ገጠመኝ አጋጥሞህ ያውቃል ?
ኬኒ ፕሪንስ :- ብዙ ባይሆን አልፎ አልፎ አዎ …
ኢትዮኪክ :- ኢትዮጵያ ተጉዙህ ታውቃለህ?
ኬኒ ፕሪንስ :– አዎ። ጊዜው ትንሽ ቆየት ቢልም በ 15 ዓመት ዕድሜ ላይ ከአባቴ ጋር ኢትዮዽያ የሚገኙ ቤተሰብቼን ልንጠይቅ ተጉዘን ነበር።
ኢትዮኪክ :- የኢትዮጵያን ምግብ ከምትወደው
ኬኒ ፕሪንስ :- ከኢትዮጵያ ባህላዊ ምግብ እንጀራ በዶሮ ወጥ ምርጫዬ ነው (በፈገግታ) እንደውም አሁን አሁን አሰኘኝ በፈገግታ …
ኢትዮኪክ :- የኢትዮጵያ ሙዚቃዎችስ?
ኬኒ ፕሪንስ :-አዎ …… የኢትዮጵያ ሙዚቃን እወዳለሁ ። ግን ብዙ ጊዜ ባላዘወትርም ።
ኢትዮኪክ :- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጫዋች የምታውቀቸው አሉ ?
ኬኒ ፕሪንስ :– አዎ ።ብሔራዊ ቡድን ደረጃ የተጫወቱትን አውቃለሁ።
ኢትዮኪክ :- አባትህ የእግር ኳስ ተጫዋች በመሆኑ ደስተኛ ነው?
ኬኒ ፕሪንስ :- አዎ አባቴም ደስተኛ ነው። የበለጠ ሊደሰት እና ኩራት ሊሰማው የሚችለው ግን የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን መለያ ለብሼ የመጫወት ዕድል ባገኝ ነው።
ኢትዮኪክ :- የእግኳስ ተጨዋች ባትሆን ?
ኬኒ ፕሪንስ :- በስፖርት ቢዝነስ ውስጥ እገባ ነበር
ኢትዮኪክ :- የአንድ ልጅ አባት እንደሆንክ አውቃለሁ፣ ለልጅህ ስለ ኢትዮጵያ የምትነግረው ?
ኬኒ ፕሪንስ :- ልጄ አሁን ገና ትንሽ ነው ፣ ግን እያደገ ሲመጣ ስለ ኢትዮጵያ የምነገው በጣም ብዙ ነገር አለ። ለልጄ ኢትዮጵያ ብዙ ታሪክ ያላት ውብ ሀገር እንደሆነች ገና በሚገባ እነግረዋለሁ።
ኢትዮኪክ :- በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ የመጓዝ ዕቅድ ይኖራል?
ኬኒ ፕሪንስ :- ሁሌም መጓዝ እፈልጋለሁ። በተለይ አሁን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከተጠራው የትውልድ ሀገሬን ለማገልገል ዝግጁ ነኝ።