የ2013 የቤትኪንግ ኢትዮዽያ የ24ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሓ ግብር የነበረው የሰበታ ከተማ እና አዳማ ከተማ ጨዋታ በሰበታ ከተማ 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ሰበታ ከተማ ዛሬ ባገኘው የሶስት ነጥብ ከ8ኛ ደረጃ ወደ 6ኛ ደረጃን በማሻሻል በቀጣይ ሁለት ጨዋታዎች የሚያገኘው የደረጃ ዕድገት አጓጊ ሆኗል።
በዛሬው ጨዋታ ሰበታ ከተማ ሶስት ነጥብ እንዲያስቆጥር ኦሴ ማዉሊ ብቸኛ ጎሉን በማስቆጠር በግሉ ያስቆጠረውን የጎል ብዛት 7 አድርሷል። በሁለተኛው ዙር ሰበታ ከተማን የተቀላቀለው ኦሴ ማዉሊ በሰበታ ከተማ የአጭር ጊዜ ቆይታው ሊሳካለት የቻለበትን ዋነኛ ምክንያት ከሱፐርስፓርት ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል ። ተጨማሪ ቆይታ እንሆ:-
ኦሴ ማዉሊ በቅድሚያ እንኳን ደስ ያለህ
” አመሠግናለሁ”
የማሸነፊያውን ጎል በማስቆጠሩ ስለተሰማው
” ጨዋታው በተወሰነ መልኩ ከባድ ነበር ፤ ይሁንና እግዚአብሔር ይመስገነው ሶስት ነጥብ ይዘን መውጣት ችለናል”
ለሰበታ ከተማ በሁለተኛው ዙር ከመቀላቀሉ አንፃር እስካሁን 7 ጎሎችን ማስቆጠር መቻሉ እና ለክለቡ ከመለወጡ አንፃር ያበረከተው አስተዋፅኦ በተመለከተ
” በርግጥ ትንሽ አስቸጋሪ ነበረ፤ ነገር ግን ለክለብህ በምን ማድረግ እንዳለብህ ካወቀክ እና በምን መልኩ መጥቀም እንዳለብኝ ካወቀክ ፤ እኔም ያደረኩት ያንን ነው። ለቡድኔ የምችለውን ሁሉ ነው እያደረኩት ማለት እችላለሁ”
ልምድ ካላቸው አማካይ ተጨዋቾች ጋር እንደነ መስዑድ እና ዳዊት ጋር መጫወቱ ለጎል ማስቆጠሩ ያደረጉትን አስተዋጽኦ በተመለከተ
” አዎ..ድንቅ ብቃት ያላቸው ተጨዋቾች ናቸው። በጨዋታ ላይ እገዛቸው ታላቅ ነው ፤ በአጭሩ ጨዋታው ለእኔ በሚቀለኝ መልኩ እንዲሆንልኝ ያደረጉት እነሱ ናቸው”
አሁን ባለው ነጥብ ሰበታ ከተማ በሁለተኝነት ደረጃ ሊያጠናቅቅ ስለመቻሉ ?
“( በፈገግታ ) …የምንችለውን እናደርጋለን ። በተቻለን አቅም ቀሪ ጨዋታዎቹን ማሸነፍ ከቻለን የእግዚአብሔር ፍቃድ ከተጨመረበት ደስተኞች እንሆናለን”
አቡበከር ናስር በተመለከተ ያለው አስተያየት
” ኦኦ…. ስለ እሱ ልናገር የምስችለው ቢኖር…. ፣ በጣም ደስተኛ ነኝ፣ ምክንያቱም አቡበከር ያሳየው የተለየ ችሎታ የተጨዋቹን ድንቅ ብቃት ያረጋገጠ ነው፣ በግሌ በጣም ተደስቻለሁ”