ቤትኪንግ ፕሪሜር ሊግ ዜናዎች

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2015 23ኛ ሳምንትና የዲሲፕሊን ውሳኔዎቹ !

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2015 23ኛ ሳምንት በሃዋሳ ከተማ በተደረጉ ጨዋታዎች አምስት ጨዋታዎች በመሸናነፍ ሶስት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ 17 ጎሎች ተቆጥረዋል።የጎሎቹ አገባብም 15 በጨዋታ ሁለት በፍፁም ቅጣት ምት ነው። በሳምንቱ 46 ተጫዋቾችና የቡድን አመራሮች በቢጫ ካርድ ሲገሰፁ አምስት ተጫዋቾችና የቡድን አመራሮች ቀይ ካርድ ተመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ ቅዳሜ ግንቦት 05 2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያ(ዎች)ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
በተጫዋችና ቡድን አመራሮች ደረጃ በተላለፉ ውሳኔዎች 7 ተጫዋቾች ላይ ቅጣት ተላልፏል። ሱራፌል አወል(ለገጣፎ ለገዳዲ)፣ ደጉ ደበበ(ወላይታ ድቻ) እና ሙሉቀን አዲሱ(ሲዳማ ቡና) ሁለተኛ ቢጫ ካርድ የሚያስጥ ጥፋት በመፈፀማቸው ቀይ ካርድ አይቶ ከጨዋታ ሜዳ የተወገዱ ለፈፀሙት ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገዱ፥ አበበ ጥላሁን(አርባምንጭ ከተማ) እና ማታይ ሉል(ኢትዮ ኤሌትሪክ) በተለያዩ 5 ጨዋታዎች የቢጫ ማስጠንቅቂያ ካርድ በመመልከታቸው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 1500 /አንድ ሺ አምስት መቶ/ እንዲከፍሉ ፥ አለልኝ አዘነ(ባህር ዳር ከተማ) በሳምንቱ ጨዋታ ሃይማኖታዊ መልእክት የሚያስተላልፍ ምስል በውስጥ ልብሱ ደርቦ ስለመልበሱ ሪፖርት የተደረገበት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ደንብ መሰረት ተጫዋቹ የገንዘብ ቅጣት ብር 3000 /ሶስት ሺህ ብር/ እንዲሁም ክለቡ የገንዘብ ቅጣት ብር 10000 /አስር ሺህ ብር/ እንዲከፍሉ፥ ዉሀብ አዳምስ/ ወልቂጤ ከተማ/ በሳምንቱ ጨዋታ ወቅት ከዳኛ እይታ ውጭ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋችን በክርን ስለ መምታቱ ሪፖርት የተደረበት ተጫዋቹ በፈጸመው ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 4/አራት/ ጨዋታ እንዲታገድና ብር 3000 /ሶስት ሺህ / እንዲከፍል ተወስኗል።
በክለቦች ደረጃ በታዩ ሪፖርቶችም የተለያዩ ውሳኔዎች ተላልፈዋል። ለገጣፎ ለገዳዲ በሳምንቱ ጨዋታ የክለቡ ከአራት በላይ ተጫዋቾች በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ክለቡ የገንዘብ ቅጣት ብር 5000 /አምስት ሺ/ እንዲከፍል ፥ ወላይታ ድቻ በ22ኛ ሳምንት ጨዋታ የክለቡ ደጋፊዎች የእለቱን ዳኛ አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸው ሪፖርት በመቅረቡ የክለቡ ደጋፊዎች ለፈፀሙት ጥፋት ክለቡ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ብር 50000/ሃምሳ ሺህ/ እንዲከፍል ፥ ኢትዮጵያ ቡና በሳምንቱ ጨዋታ የክለቡ ተጫዋቾች የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታድየም መልበሻ ክፍል ሁለት በሮች ስለመስበራቸው ሪፖርት የተደረገ ሲሆን ክለቡ የተሰበሩትን በሮች እንዲያሰሩ ወይም የዩኒቨርስቲው አሰተዳደር የሚያቀርበውን የንብረትን ዋጋ እንዲከፍል ተወስኗል፡፡
በተጨማሪም በፕሪምየር ሊጉ አ.ማ. የተቋቋመው ቴክኒካል ኮሚቴ የ23ኛ ሳምንት እግር ኳስ ጨዋታ አንዱ በሆነው የኢትዮጵያ መድን ና ሲዳማ ቡና ግጥሚያ ዙሪያ ምርመራ እያደረገበት በመሆኑ የኮሚቴው የቅድመ ምርመራ ውጤት እስኪታወቅ ድረስ የጨዋታው ውጤት እንዳይጸድቅ እና ከጨዋታው ጋር የተያያዙ የዲሲፕሊን ውሳኔዎች ውጤቱ ከታወቀ በኋላ እንዲታዩ የውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ ወስኗል።