ዜናዎች

” በአፍሪካ ዋንጫ በማለፋችን በጣም ነው የተደሰትነው ፣ደስታው ለእኛ ለኢትዮዽያዊያን ከኳስም በላይ ነውና” ➖ያሬድ ባዬ

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከምድቡ 2ኛ በመሆን ለ33ኛው የካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ከምስራቅ አፍሪካ ከሱዳንን ጋር ማለፏን አረጋግጧል። ዛሬ በአቢጃን ላይ ከኮትዲቯር አቻቸው ጋር የተጫወቱት ዋልያዎቹ 3ለ1 በሆነ ውጤት እስከ 83ኛው ደቂቃ ተመርተው የነበረ ቢሆንም በመሀል ዳኛው ድንገተኛ የጤንነት ችግር ጨዋታው በመቋረጡ እና በውጤቱ መሠረት ዋልያዎቹ ለአፍሪካ ዋንጫ አልፈዋል።በዛሬው ጨዋታው በዋልያዎቹ በኩል የመጀመሪያው ጎል የተቆጠረው ከጥንቃቄ ጉድለት የነበረ ሲሆን በተቃራኒው የኮትዲቯር ብሔራዊ ቡድን የአየር ላይ ኳሶች የተሻሉ በመሆናቸው ከእረፍት በፊት በሁለተኛው እና በ19ኛው ደቂቃዎች ጎሎች አስቆጥረው የመጀመሪያው አጋማሽ በኮትዲቫር 2 ለ 0 የበላይነት ተጠናቋል።
ከእረፍት መልስ ተቀይሮ የገባው ሽመክት ጉግሳ ለጌታነህ ግሩምና ያለቀላት ኳስ አመቻችቶ በመስጠቱ ጌትነት ከበደ በ74ኛው ደቂቃ ጎል አስቆጥሮ የነበረ ቢሆንም የጌታነህ ጎል በተቆጠረበት የአንድ ደቂቃ ልዪነት ኮትዲቫር ሶስተኛውን ጎሏን በማስቆጠር የዋልያዎቹን የማለፍ ተስፋ ድንጋጤ ውስጥ ከቶቷል።
በአንፀሩ ማዳጋስካር ከኒጀር የሚያደርጉትን ጨዋታ ለዋልያዎቹ የማለፍ ሌላኛው ዕድል ነበርና የሁለቱንም ጨዋታ ውጤት አጓጊ አድርጎት እስከ 83ኛው ደቂቃ ዘልቋል።
ሆኖም በ83ኛው ደቂቃ ጨዋታውን ሲመሩ የነበረት ጋናዊው ዳኛ ራሳቸውን በመሣታቸው ጨዋታው ለ11 ደቂቃዎች ከተቋረጠ በኃላ አራተኛ ዳኛው ኮትዲቯራዊ በመሆናቸው ጨዋታውን ማጫወት ስለማይችሉ በኮትዲቯር 3 ለ 1 ውጤት ተጠናቋል።
በተመሳሳይ ሰአት በማዳጋስካር ሜዳ የተጫወቱት ኒጀር እና ማዳጋስካር 0 ለ 0 አቻ በመውጣታቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ሁለተኛ ሆኖ ማለፉን አረጋግጧል።ውጤቱን ተከትሎ ቀድማ ያረጋገጠችው ኮትዲቯር ምድቡን በ13 ነጥብ በመምራት የአፍሪካ ዋንጫውን ስትቀላቀል፣ዋልያዎቹ የምድብ 11 ማጣሪያውን በ9 ነጥብ 2ኛ ሆነው በማጠናቀቅ ኮትዲቫርን ተከትለው ለአፍሪካ ዋንጫ አላፊ ሆነዋል ።
ከዛሬው ጣፋጭ ውጤት በኃላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጠንካራ የኃላ ደጀን ያሬድ ባዬ ለኢትዮ ኪክ የደስታ ስሜቱን በዚህ መልኩ ገልፆልናል
” በአፍሪካ ዋንጫ በማለፋችን በጣም ነው የተደሰትነው። ደስታው ለእኛ ለኢትዮዽያዊያን ከኳስም በላይ ነውና። በውጤቱ እጅግ ደስ ብሎኛል ። በርግጥ ብዙ ስራ ይጠብቀናል። የተሻለ ብሔራዊ ቡድን እንዲሆን ጠንክረን በቀጣይ ከዚህ በላይ እንሰራለን ። ለአፍሪካ ዋንጫም የተሻለ እና ጥሩ ተፎካካሪ ቡድን ሆነን እናቀርባለን ብዬ አስባለሁ ” በማለት ያሬድ ባዬ ደስታውን ገልፆልናል።