የኢትዮጵያ የቻን ብሔራዊ ቡድን በአልጄርያ አስተናጋጀነት በተከናወነው የአፍሪካ ሀገራት ሻምፒዮና (ቻን) ውድድር ላይ ያደረገውን ተሳትፎ አስመልክቶ የልዑክ ቡድኑ አባላት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አመራር ኮሚቴ አባላት በዛሬው ዕለት ሐሙስ ጥር 25 በኢሊሊ ሆቴል ሪፖርት አቅርበዋል።
በሪፖርቱ የተባሉት ጉዳዮች የሚከተሉት ቢሆን ግምገማ የተደረገው ሐሳብ ከማውራት ባለፈ ለብሔራዊ ቡድኑ ቀጣይ አሁን ላይ እረግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም።
የዛሬው ሪፖርት እና የግምገማ መድረክን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ እና ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን የመሩት ሲሆን የሥራ አመራር ኮሚቴ አባላት ፣ የልዑክ ቡድኑ መሪ እና የቴክኒክ አሜካሪ ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ዳኛቸው ንገሩ ፣ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተና የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ፣ የማኔጅመንት አባላት እንዲሁም የተለያየ የስራ ሚና የነበራቸው አባላት ተገኝተውበትም ነበረ።
በቅድሚያ የብሔራዊ ቡድናችን ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በውድድሩ ዙርያ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን በሪፖርታቸው ቅድመ ውድድር ላይ ስለተሰሩ ስራዎች ፣ በሞሮኮ ስለነበረው ቅድመ ዝግጅት ፣ በውድድሩ ላይ ስለነበሩ ጉዳዮች ዝርዝር ሪፖርት አቅርበዋል። ስለ ተጫዋቾች መረጣ ፣ ከሞሮኮ ጋር የዝግጅት ጨዋታ በማድረግ ተጫዋቾች ምዘና ስለመደረጉ ፣ በዝግጅት ጨዋታዎቹ የተለያዩ የጨዋታ ሲስተሞች እንዲሞክሩ መደረጉን ፣ በዳታ እና ቪድዮ ትንታኔ ከጨዋታ በፊት እና በኋላ ለተጫዋቾች በማሳየት ቡድኑን ለማዘጋጀት ጥረት መደረጉን ፣ ለወጣት እና አዳዲስ ተጫዋቾች እድል መሰጠቱን ያወሱት አሰልጣኝ ውበቱ ከውድድር በፊት እና በውድድር ወቅት የተከሰቱ የተጫዋቾች ጉዳቶች ፣ የጉዞ ችግሮች ፣ የልምምድ ሰዓት መዛባት የፈጠሩት መሰላቸት ፣ በሊጉ ጥሩ አቋም ላይ የነበሩ ተጫዋቾች ብቃታቸውን የማሳየት ክፍተት እና የመሳሰሉት እንደ ተግዳሮት አንስተዋል። በውድድሩ ላይ የነበረውን የቡድኑ ብቃትም በቁጥር በተደገፈ መልኩ አቅርበው ነበር።
በመቀጠል የአካል ብቃት ባለሙያ ዶ/ር ዘሩ በቀለ ባቀረቡት ሪፖርት በዘርፉ የተከናወኑትን ተግባራት ለኮሚቴው አብራርተዋል። የተጫዋቾች የስብ ልኬት የተጫዋቾች ጥሪ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ መከናወኑንና በዛም መሠረት ማስተካከያ መደረጉ ፣ የGPS ልኬት በማከናወን የጫዋቾች የፍጥነት እና ተያያዥ የአካል ብቃት ሁኔታዎችን በማከናወን ለተጫዋቾች ትምህርት መሰጠቱን ፣ የማገገሚያ ስርዓቶችን በመጠቀም ተጫዋቾች እንዲያገግሙ የማድረግ ስራ ስለመሰራቱ ካነሷቸው ነጥቦች መካከል ናቸው።
በማስከተል የሥነ-ምግብ ባለሙያው ዳንኤል ክብረት በስነ ምግብ ዙርያ የተሰሩ ተግባራት ላይ ባቀረበው ሪፖርት ልኬት በማከናወን ተጫዋቾችን የማስተማር ስራ በማድረግ ቁጥጥር እንደሚደረግ ፣ ባረፉባቸው ሆቴሎች የምግብ ዝግጅት ፣ የሚጠቀሟቸው ግብአቶች ፣ ይዘቶች እና ንፅህና ላይ ቁጥጥር መደረጉን ፣ የሽንት ምርመራ በማድረግ ተጫዋቾች የሚያስፈልጋቸው የፈሳሽ መጠንን በመለየት እንዲወስዱ መደረጉን ፣ በጉዞ ላይ የተጫዋቾችን የአመጋገብ ክፍተት እንዳይፈጠር ጥረት መደረጉን በሪፖርተቱ ላይ ከጠቀሳቸው መካከል ናቸው።
የፐርፎርማንስ ተንታኝ ኤልሻዳይ ቤከማ በውድድሩ ወቅት የነበረው የቡድኑ ብቃት በቪድዮ ትንተና እና በዳታ መከናወኑን ገልፆ በዳታ ላይ ተመስርቶ የቡድኑ ጠንካራ ጎን እና ደካማ ጎን እንዲሁም የተጋጣሚዎች ብቃት መታየቱን ገልጿል። ለቀጣይ ውድድሮችም ለተጫዋቾች መማርያ እንደሚሆን ማብራርያውን አቅርቧል።
ከህክምና ጋር የተያያዘውን ሪፖርት የኢ/እ/ፌ የህክምና ክፍል ዳይሬክተር ዶ/ር ሳሙኤል የሺዋስ ያቀረበ ሲሆን ከህክምና ጋር የተያያዙ ስራዎች ለማከወን የሚያስፈልጉ ባለሙያዎችን በማዋቀር እና ለቁሳቁስ ግዢዎች አስፈላጊ በጀት ማዘጋጀት ፣ ከውድድሩ በፊት ጀምሮ የህክምና አገልግሎት እና ክትትል መሰጠት ፣ ከስፖርት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የሌላቸው ህመሞች ፣ የስፖርት ጉዳቶች ምርመራ እና ትሪትመንት ፣ ከሃይድሬሽን ፣ ከኮቪድ-19 ፣ ከፊዝዮቴራፒ ፣ አመጋገብ አንፃር እንዲሁም የሜዳ ላይ የጨዋታ እና ልምምድ ላይ የህክምና አገልግሎት የመስጠት ስራ መከናከኑን ፣ የላብራቶሪ ፣ ኤምአርአይ እና ሌሎች አገልግሎቶች መሰጠታቸውን እና ውድድሮች ካለቁ በኋላም ጉዳት ላይ ያሉ ተጫዋቾች ክትትል እንደሚቀጥል ገልጿል።
የልዑክ ቡድኑ መሪ እንዲሁም የቴክኒክ አማካሪ ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ዶ/ር ዳኛቸው ንገሩ በተለይም ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ አተኩረው ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን ቡድኑ በሞሮኮ ያደረገው ዝግጅት እና የአልጄርያው ውድድር ላይ የነበራቸውን ምልከታ ፣ ጠንካራ ጎኖች እና ክፍተቶች እና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ሰፋ ባለ ማብራርያ አቅርበዋል። ክፍተት በነበረባቸው የሜዳ ክፍሎች ላይ በተናጠል አለመስራት ፣ የማጥቃት ስነ ልቦና ላይ ስልጠና ያለመስጠት ፣ የጨራረስ ድክመት ፣ ደክመው የታዩ ተጫዋቾች ለመቀየር ረጅም ጊዜ የመውሰድ እና ቀጣይ ጨዋታ ላይ ለውጥ አለማድረግ ፣ ተጫዋቾች የአሰልጣኞችን ስልጠና የመቀበል ክፍተት ፣ ጨዋታን በመቆጣጠር መሪነትን አለማስጠበቅ ፣ በልምምዶች ላይ ድክመቶቻንን ከማሻሻል ይልቅ ጠንካራ ጎናችን ላይ በተደጋጋሚ የማተኮር ፣ በሊጉ ጥሩ ብቃት ላይ የነበሩ ተጫዋቾች በውድድሩ ላይ አቋም ወርዶ መታየት ፣ በተጫዋቾች ላይ ከውጤት ማጣት በኋላ የቁጭት ስሜት አለመታየት እና የመሳሰሉትን በክፍተትነት እንደመለከቱ ከገለጿቸው መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
ከልዑክ ቡድኑ ሪፖርት በማስከተል የስራ አመራር ኮሚቴ አባላት በቀረበው ሪፖርት ላይ እና ብሔራዊ ቡድኑ በውድድሩ ላይ የነበራቸውን ምልከታ ፣ አስተያየት እና ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን በአባላቱ በተለይም በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ምላሽ ቢሰጥም በቀጣይ በቡድኑ ላይ በትክክል ለውጥ የማይፈጥር ከሆነ ትርፉ ድካም ነው።
በዛሬው ሪፖርት እና ግምገማ ባሻገር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ያለበትን ሁኔታ የሚያሳይ ሰነድ በቴክኒክ አማካሪ ቦርድ ፣ በሰብሳቢው ዶ/ር ዳኛቸው ንገሩ አስተባባሪነት ከአሰልጣኞች ቡድን አባላትና ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ችግር ፈቺ እና የወደፊት ጉዞን አመላካች በሆነ መልኩ በአጭር ጊዜ በማዘጋጀት የምክክር መድረክ እንዲዘጋጅ ውሳኔ ተላልፏል።
በተጨማሪም ቀጣይ ብሔራዊ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከጊኒ ጋር በተከታታይ ጨዋታዎች የሚያደርግ መሆኑን በማውሳት ብሔራዊ ቡድኑ ከቻን ስህተቱ በመማር የምድብ መሪነቱን አስጠብቆ የአፍሪካ ዋንጫ ተከታታይ ተሳትፎን እንዲያሳካ ትኩረት ተሰጥቶ ዝግጅት እንዲደረግ አቅጣጫ ይሰጣል ተብሏል።
የግምገማ መድረኩ ከወረቀት እና ከማውራት ባለፈ ለብሔራዊ ቡድኑ ቀጣይ ጨዋታ የማይጠቅም ከሆነ ምን ይፈይዳል?