ዜናዎች

በአዲስ አበባ ስታዲየም ዙሪያ ያሉ -ሱቆችና የመኪና አከራዮች በ15 ቀናት ውስጥ ሊነሱ ሲሆን- ዙሪያውም ሊታጠር ነው !

 

🕳 የስታዲየሙ ዕድሳት አራት ዓመታት ሊያስቆጥር ተቃርቧል!

👇
በቀድሞ መጠሪያዉ ቀኃሥ ስታድየም በአሁኑ ስያሜዉ የአዲስ አበባ ስታዲየምን ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን አሟልቶ ለማጠናቀቅ ቀሪ ሥራዎች ከሦስት ወራት በላይ እንደማይፈጅ በባሕል እና ስፖርት ሚንስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ከዶይቸ ቬለ (DW) ጋር ከቀናት በፊት ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሲናገያያለ በአንፃሩ የአዲስ አበባ ስታዲየም ዕድሳት አሁንም አዲስ ነገር ይዞ በመቀጠል በዙሪያው ያሉ ሱቆች በ15 ቀናት እንዲለቁ እና የመኪና አለማማጆችም እንዲነሱ ሊደረግ መሆኑን የኢትዮኪክ ታማኝ መረጃዎች ጠቁመዋል።

ለሀገሪቱ ለረጅም ጊዜ በብቸኝነት ያገለገለው እና በበርካቶቾ ዘንድ እምቅ እና አይረሴ ትዝታዎችን ይዞ በሴካፋ ጮቤ የተረገጥንበት ከእንደተመኘሁት አገኙዋት እስከ ይትባረክ ዘላለም ተብሎ የተዜመበት ስፍራ የአዲስ አበባ ስታዲየም በዕድሳት ሰበብ አራት ዓመታት ሊያስቆጥር ተቃርቧል።

በተለይ ደግሞ በታሪክ ሶስት አፍሪካ ዋንጫ ያስተናገደበት መጀመሪያዉን ያስተናገደዉን የአፍሪካ ዉድድር ዋንጫዉ የቀረበት ስፍራ ፣ ከአፄ ሀይሌ ስላሴ እስከ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ድረስ የረገጡት ቦታ፣ ከክቡር ይድነቃቸዉ ተሰማ እስከ ሳላዲን ሰኢድ የነገሱበት ፣ ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ በአዘቦት ቀንም የተመልካቹ ረጅም ሰልፍና የማይጠገቡ የደጋፊዎችን ጨዋታ የተመለከቱበት በካታንጋ ፣ በዳፍ ናፋሲካ በር ፣በሚስማር ተራ ፣በአበበ ቢቂላ በር ፣ከማን አንሼ ጥላ ፎቅና ክብር ትሪቡኑ ትዕይንቶች የተሞላበት ይህ የአዲስ አበባ አሁን ላይ ዳግም የሚመጣበት ቀን እጅጉን ርቆ ይገኛል።

በስታዲየሙ ሐይማኖታዊ በዓላት የተካሄዱበት ፣አትሌቶች በኢትዮጵያ ሻምፒዮና የሚመረጥበት፣ በታዋቂ ድምፂያኖችና በባንዶች ታላላቅ ኮንሰርቶች የተካሄደበት ፤ታማኝ በየነ ህዝብ ለህዝብ ላይ ፖለቲካዊ ይዘት ዘፈኖችና ንግግሮችን ያረገበት ፣ በኢህአፖ ዘመን ትልቅ መሸሸጊያ የነበረበት ታሪካዊ ስፍራ ዳግም ለማየት አሁን ላይ ከባድም ሆኗል።

የኢትዮ ኪክ መረጃዎች እንደጠቆሙት ከሆነ በዙሪያው ያሉ ሱቆች፣ምግብ እና መጠጥ ቤቶች ዘርፍ ቀይሩ ተብለው ማስጠንቀቂያ ተሰጧቸው የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ግን ሁሉም በዙሪያው ያለው የስፖርት ትጥቆች፣ የትርጉም ቤቶች ፣የባህላዊ ሱቆች የመኪና እና ሞተር አለማማጆች ጨምሮ ዙሪያው ሊታጠር መሆኑ ተሰምቷል። በስታዲየሙ ዙሪያ ያለው እና ፌዴሬሽኑ በቅርቡ የግሉ ያደረገው የነዳጅ ማድያም በዚሁ መልኩ ተካቷል።
የአዲስ አበባ ስታዲየም ዙሪያ ያሉ ሱቆች በ15 ቀናት ለቀው እንዲወጡ እና ሙሉ ለሙሉ ዙሪያ መታጠሩ ለዕድሳት ይሁን ተያያዥ ጉዳዮ ስለመሆኑ ፌዴሬሽኑ በይፋ የተናገረው መረጃ የለም። በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ መረጃዎች ሲደርሱን እናቀርባለን።