ዜናዎች

በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወቱ ላለፈው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ነገ በሮማ የመታሰቢያ እግርኳስ ይደረጋል !

 
በጣሊያኖቹ ኤሲ ሚላን እና ቤኔቬንቶ ወጣት ቡድኖች ተጫዋች የነበረው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ሰዒድ ቪዚን ህይወቱ በአሳዛኝ ሁኔታ ካለፈ አንድ ሳምንት የተቆጠሩ ሲሆን እሱን በማሰብ የመታሰቢያው የእግርኳስ ውድድር ተዘጋጅቷል ።
በሀገረ ኢትዮጵያ ተወልዶ በ7 ዓመቱ በጣልያኖቹ የኖቼራ ኢንፌሪዮር ተወላጆች በሆኑት የማደጎ (ጉዲፈቻ) ቤተሰቦቹ ጋር ያደገው1 ሰዒድ ቪዚን በእግር ኳስ ተስፋ የተጣለበት ታዲጊ የነበረ ቢሆንም በ20 አመቱ በዘረኝነት ሰለባ በመሆን ራሱን አጥፍቷል።
ታዲያ በታዳጊነት ዕዴሜው በዘረኝነት ጥላቻ ሰለባ በመሆን ራሱን ላጠፋው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ወጣት ሰዒድ ቪዚን በጣልያን የሚገኙ ኢትዮዽያውያን የመታሰቢያ ውድድር ነገ (ቅዳሜ) አዘጋጅተዋል።
በኢትዮ ሮማ የስፖርት እና የባህል ማህበር አዘጋጅነት እና በጣሊያን ከሚገኘው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጋር በመተባበር የሚደረገው የእግርኳስ ጨዋታ ነገ ቅዳሜ በ12 : 00 ሰዓት በፒዮኒየሪ ስታዲየም የሚካሄድም ይሆናል።
የመታሰቢያ ውድድሩን ያዘጋጁት የኢትዮ ሮማ የስፖርት እና የባህል ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ አሌሳንድሮ ባቸር ለኢትዮኪክ የነገውን የመታሰቢያ ዝግጅት በተመለከተ ይህን ብለውናል
” በተፈጠረው ነገር በጣም አዝነናል። ይህን ምክንያት በማድረግ በሰዒድ ስም የመታሰቢያ እግርኳስ እናደርጋል ። ከዚሁ ጋር በሰዒድ መታሰቢያ ቀን አብረን የበለጠ ትኩረት ለመስጠት ያሰብነው ይሄ ችግር እዚህ ጣሊያን በጣም ብዙ ልጆች እንደሱ ዓይነትችግር ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ስለዚህ በቀጥታ የታሰበው የወዳጅነት ጨዋታ ሲሆን ቡድኖቹ ደግሞ በአጠቃላይ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ቡድን ከእኛ ጋር እንዲጋጠሙ ነው። ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት የዕሊና ፀሎት እና መልዕክት ይኖራል። በዚህ የመልዐክት ሂደት ላይ የሰዒድ አባት እና እናት ( አሳዳጊዎቹ ) በቦታው ባይገኙም በቀጥታ ቪዲዮ የሚገኙ ይሆናል።  በሮማ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እና ታላላቅ እንግዶች በመታሰቢያው የእግር ኳስ ውድድሩ ላይ የሚገኙም ይሆናል። እንዳልኩት የእኛ ዓላማ ከዚሁ ጋር በጣም ብዙ ህፃናቶች በተመሳሳይ ችግር ውስጥ የሚገኙ አሉ። እኛ ጋር ለምሳሌ 20 የሚጠጉ እኛ  በስፓርት ውስጥ ሆነው ፤ በብቸኝነት ህይወት ውስጥ እንዳይሆኑ የምንረዳቸው ታዳጊዎች አሉ። የኢትዮ ሮማ ከተመሠረተበት እ.ኤ.አ 2009 ጀምሮ ይህንን ተግባር እያደረገ ይገኛል። በገቢ ደረጃ በጣሊያን የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን  ነዋሪዎች ፣ትንሽ ከኤምባሲው ና ከተለያዩ በዓመት ከምናደርጋቸው ፌስቲቫል ድጋፎች ክሚገኝ ገቢ ታዳጊዎቹን የምንረዳው። በቀጣይም በዚህ ጉዳይ የስፓርት ማህበሩ ችግር ውስጥ የሚገኙትን በኢትዮዽያዊያን፣ ኤርትራውያን እና የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ታዳጊዎች በስፓርትና ከጭንቀት እንዳይገቡ የምንችለውን ስራዎች በመስራት እንቀጥላለን “
በማለት የኢትዮ ሮማ የስፖርት እና የባህል ማህበር ፕሬዝዳንት አሌሳንድሮ ባቸር  ለኢትዮኪክ ተናግረዋል