የባሕር ዳር ዓለም-አቀፍ ስታዲየም የማሻሻያ ግንባታ እየተካሄደ ሲሆን ሲጠናቀቅ በካፍ መመዘኛ ካታጎሪ 4 ላይ (የካፍ የመጨረሻ የጥራት ደረጃ መመዘኛን የሚያሟላ ሆኖ ይጠበቃል ሲል ፌዴሬሽኑ ዘግቧል።
ይህን በማስመልከት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና ክለብ ላይሰንሲግ ዲፓርትመንት የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ግንባታ ያለበትን ደረጃ ምልከታ አድርገዋል።
ካለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ ግንባታው እየተከናወነ የሚገኘው ስታዲየሙ ከዚህ ቀደም በካፍ አስተያየት የተሰጠባቸው አስፈላጊ ክፍሎች ግንባታ እየተከናወነ ሲሆን ከዚህ ቀደም የነበሩትንም ደረጃቸውን የማሳደግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የፌዴሬሽኑ መረጃ ያመለክታል።
በተጨማሪም የመጫወቻ ሜዳ የፊፋ እና ካፍ ፍቃድ ባለው የፈረንሳዩ ግሪጎሪ ኢንተርናሽናል እየተከናወነ በሚገኘው የመጫወቻ ሜዳ ሥራ ከዚህ በፊት የነበረውን ሜዳ ሙሉ ለሙሉ በማንሳት እየተሰራ መሆኑ ሲገለፅ የልምምድ ሜዳ
ሥራው ከመጫወቻ ሜዳው ሁለት የልምምድ ሜዳዎችን የሚያካትት ሲሆን ከመጫወቻ ሜዳው ጋር በተመሳሳይ የጥራት ደረጃ የሚከናወን ይሆናልም ተብሏል።
ከዚሁ ጋር የስታዲየም ዙርያ እና ቅጥር ግቢ ወደ ስታዲየሙ ግቢ የሚያስገቡ ከዚህ ቀደም የነበሩት ሁለት በሮች ወደ አምስት እንዲያድጉ መደረጉ ሲገለፅ ከውጪ ወደ ውስጥ ከገቡ በኋላ ወደ ቪአይፒ፣ ቪቪአይፒ፣ ሚዲያ እና የቡድኖች መኪና ማቆምያ መግቢያዎች እየተሰራ እንደሚገኝ የደጋፊዎች መኪና ማቆሚያ እና እግረኛ መግቢያም ተለይቶ ሥራ መጀመሩን እና የዲጂታል ቲኬቲንግ መቆጣጠርያ ለመስራትም በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ተገልፆልናል።
ስታዲየም በአሁኑ ሰዓት ሁለት አሳንሰር (ሊፍት) ግንባታ የተከናወነ ሲሆን የሚቀረው የሊፍት ገጠማ ብቻ ይሆናል ተብሏል። ይህም ሊፍት የሚዲያ፣ የቪአይፒ እና ቪቪአይፒ እንግዶች የሚጠቀሙበት ይሆናል።
ስታዲየሙ በአንድ ጊዜ አራት ቡድኖችን ለማስተናገድ በሚያስችል መልኩ አራት መልበሻ ክፍሎች እና የዳኞች መልበሻ ክፍል በግንባታ እንደሆነ እና በሁሉም ክፍሎች ላይ የአየር ማመጣጠኛ (AC) መስመር ዝርጋታ ተጀምሯል።
የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የማሻሻያ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ በካፍ መመዘኛ ካታጎሪ 4 ላይ (የካፍ የመጨረሻ የጥራት ደረጃ መመዘኛን የሚያሟላ) ሆኖ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። ይህም ማለት የብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎችን ጨምሮ እስከ ፍፃሜ ድረስ ያሉ የአፍሪካ የክለብ ውድድሮች እንዲሁም የአፍሪካ ዋንጫን የመሳሰሉ ውድድሮችን የማስተናግድ አቅም እንደሚኖረው የፌዴሬሽኑ መረጃ ያመለክታል።