ቤትኪንግ ፕሪሜር ሊግ ዜናዎች

“ግብ ጠባቂዎቹን ገልብጠን አጥቂ ቦታ ላይ አሰልፈናል ፤ እንደውም ተሳስተው ፔናልቲ ሳጥን በእጅ እንዳይዙ እያለን እየሰጋን ነበረ” – አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው

በቤትኪንግ የ19ኛው ሳምንት የትላንት ምሽቱ ጨዋታ ወላይታ ድቻ አንድም ተቀያሪ ተጨዋች ሳይኖረው በ11 ተጨዋቾች ብቻ ሃዋሳ ከተማ ገጥሞ ጨዋታን በ3 ለ 2 ተሸናፊነት አጠናቋል። ለችግሩ በዋነኝነት የኮቪድ ወረርሸኝ እና የተጨዋቾች ተደራራቢ ጨዋታ ለጉዳት በቀላሉ መጋለጥ ዋነኞቹ ምክንያቶች ናቸው። በትላንቱ የምሽት ጨዋታም የታየው ይኸው ነው። በወላይታ ድቻ በኩል በአጥቂ ቦታ ላይ ግብ ጠባቂዎቹ መክብብ እና አብነት አሰልጣኙ ገልብጦ እንዲያጫውት ተገዷል።በአጠቃላይ አምስት ጎሎች ከተቆጠሩበት የምሽቱ ጨዋታ የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ከጨዋታው ሠጠናቀቅ በኃላ ለሱፐር ስፖርት የሚከተለውን ብሏል።
ከተቆጠሩት ጎሎች የትኛው ነበር ያበሳጨህ?
“ሶስተኛው እና የመጀመሪያው አበሳጭቶኛል። በተለይም ደግሞ ሶስተኛው ጎል አበሳጭቶኛል። ምክንያቱም 1ኛ ጨዋታው ተጠናቆ ነበር፤ 2ኛው ከፍተኛ ትኩረቴ ማጣት ነበር የተስተዋለው። በቀላሉ መቆጣጥር የምትችለው ኳስ ሲገባ ትንሽ ያበሳጫል። ሌላኛው ተጨርፎ የገባ ነው ምንም ማድረግ አይቻልም።
በፊት መሥመር ላይ ስለአሰለፋቸው ግብ ጠባቂዎች
” (በፈገግታ )የሚችሉትን አድርገዋል። ግብ ጠባቂዎቹን ገልብጠን አጥቂ ቦታ ላይ አሰልፈናል ፤ እንደውም ተሳስተው ፔናልቲ ሳጥን በእጅ እንዳይዙ እያለን እየሰጋን ነበረ…(በፈገግታ) በጥቅሉ ግን የሚችሉትን አድርገዋል። እንደ ቡድን ልጆቹ የሚችሉትን አድርገዋል ። በጣም ታግለዋል። ሁለት ግብ ማስቆጠር በራሱ ትልቅ ነገር ነው። የገቡብን ኳሶች ያን ያክል ተለፍቶባቸው የመጡ ሳይሆኑ በእኛ የትኩረት ማጣት የገቡ ስለሆኑ ብዙም ቅር አላለኝም። ልጆቹ ታግለዋል”
ከጨዋታው በፊት እንደዚህ ጥሩ ጨዋታ ጠብቀህ ነበር ፣ (ሁለት ግብ ጠባቂ አጥቂ አድርጎ ያለምንም ተቀያሪ ተጨዋቾች ከመሰለፉ አንፃር?
“አንዳንድ ጊዜ ምን አለህ መሠለህ እንደዚህ አይነት ነገሮች ሲያጋጥሙ ልበ ሙሉ መሆን ያስፈልጋል። ምንም አይነት ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ ፤ እነዛን ችግሮች ግን ተቃቁሞ ማለፍ ማሸነፍ ያስፈልጋል። ትልቁ አቅም የሚባለውም ይኸ ነው። በተሳካ ሁኔታ ላይ መረማመድ ሳይሆን በፈተናዎች ላይ አሸናፊ ሆኖ ማለፍ ነው ትልቁ ብቃት የሚባለው። እናም ከተጫዋቾቼም ጋር ስናወራ የነበረው ያንን ነው ። በርግጥ ጥረት እንዲሚያደርጉ ገምተን ነበር በመጀመሪያም ነገር ግን ከገመትኩት በላይ ነው እንቅስቃሴው ። ያን ያክል ሁለት ጎል እናስቆጥራለን ብዬ አላሰብኩም ። በጨዋታው የአቻ ውጤት ይዘን እንወጣለን ብዬ ገምቼ ነበር ።
ከዚህ መነሻነት ተጨዋቾቼ በደንብ ተጋድለው እንደሚጫወቱ ግምት ነበረኝ። እንደውም እንቅስቃሴው ከገመትኩት በላይ ነው። ሁለት ጎል እናገባለን ብዬ ባላስብም ከጨዋታው ቢያንስ ነጥን ይዘን እንወጣለን የሚል እምነት ነበረኝ።”