ቤትኪንግ ፕሪሜር ሊግ ዜናዎች

የ2016 ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አስራ ሰባተኛ ሳምንት የዲሲፕሊን ውሳኔ!

 

🕳ድሬዳዋ ከተማ ክለብ ደጋፊዎች ድንጋይ ወደ ሜዳ ስለመወርወራቸው ሪፖርት ቀርቦ ሃያ አምስት ሺህ እንዲከፍል ተወስኗል!

👇

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ መጋቢት 02 2016 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያ(ዎች)ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

በሳምንቱ መርሃ ግብር በተደረጉ ጨዋታዎች አምስቱ በመሸናነፍ ቀሪ ሶስቱ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ 16 ጎሎች በ13 ተጫዋቾች ተቆጥረዋል። 46 ቢጫ ካርድ ለተጫዋቾችና ቡድን አመራሮች ሲሰጥ ሶስት ቀይ ካርድ ተመዝግቧል።

በሳምንቱ በአምስት ተጫዋቾች እና አንድ አሰልጣኝ ላይ የዲሲፕሊን ውሳኔ ተላልፏል። አቤል አሰበ(ድሬደዋ ከተማ) ሁለተኛ ቢጫ ካርድ የሚያስጥ ጥፋት በመፈፀሙ በቀይ ካርድ ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ 1 ጨዋታ እንዲታገድ ፥ አድናን ረሻድ(አዳማ ከተማ) እና ቢንያም ፍቅሩ(ወላይታ ድቻ) የተጋጣሚን ተጫዋች በመማታት በቀይ ካርድ ከጨዋታ ሜዳ የተወገዱ ለፈፀሙት ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 4 ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 3000 /ሶስት ሺ/ እንዲከፍሉ ፥ አስቻለው ታመነ(መቻል) እና ያሬድ ካሳዬ(ኢትዮጵያ መድን) በተለያዩ 5 ጨዋታዎች የቢጫ ማስጠንቀቂያ የተመለከቱ ሲሆን ተጫዋቾቹ ለፈፀሙት ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 1500 /አንድ ሺ አምስት መቶ/ እንዲከፍሉ እንዲሁም አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ/መቻል/ ክለቡ ከከባህር ዳር ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ በተጋጣሚ ቡድን አሰልጣኝ ላይ ለጠብ የሚያነሳሳ የስነምግባር ድርጊት ስለመፈፀማቸው ሪፖርት ቀርቦ አሰልጣኙ በዕለቱ ለፈፀሙት ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 4/አራት/ጨዋታ አንዲታገዱና በተጨማሪም ብር 5000/አምስት ሺህ/ እንዲከፍሉ ተወስኗል።

በሶስት ክለቦች ላይም የዲሲፕሊን ውሳኔ ተላልፏል። ከወልቂጤ ከተማ ተጫዋቾች ሄኖክ ኢሳያስ፣ ጌቱ ሃ/ማርያም፣ ዳንኤል ደምሴ፣ አዳነ በላይነህ እና መሳይ ጳውሎስ ፥ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጫዋቾች በረከት ግዛው፣ ዮናስ ለገሰ፣ ሐብታሙ ሸዋለም፣ ሱሌማን ሀሚድ እና ኪቲካ ጅማ እንዲሁም ከድሬደዋ ከተማ ሔኖክ አንጃው፣ አቤል አሰበ፣ ሄኖክ ሀሰን እና መሀመድ አብዱላጢፍ በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ሶስቱ ክለቦች የገንዘብ ቅጣት ብር 5000 /አምስት ሺ/ እንዲከፍሉ ሲወሰን በተጨማሪም ድሬዳዋ ከተማ በሳምንቱ ጨዋታ የክለቡ ደጋፊዎች ድንጋይ ወደ ሜዳ ስለመወርወራቸው ሪፖርት ቀርቦ የክለቡ ደጋፊዎች በዕለቱ ለፈፀሙት ጥፋት ክለቡ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ብር 25000/ሃያ አምስት ሺህ/ እንዲከፍል ተወስኗል።