ዜናዎች

የፕሪሚየር ሊግ ተጫዋቾች የቅድመ ውድድር ጤና ምርመራ ሊጀመር ነው !

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስር ተመዝግበው በፕሪምየር ሊግ ቤትኪንግ ውድድር የሚጫወቱ ተጫዋቾች የ2014 ዓ.ም የውድድር ዘመን ከመጀመሩ በፊት ተጫዋቾች የጤና ምርመራ ማድረግ እንዳለባቸው የሚያስገድድ ህግ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ ከአሁን በፊት ተጫዋቾች ከክለብ ክለብ ሲዘዋወሩም ሆነ ውል ሲያድሱ የጤና ምርመራ እንዲያደርጉ የሚያስችል አስገዳጅ ህግ ባለመኖሩ ተጫዋቾች በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ለችግር ሲዳረጉ ተስተውሏል፡፡
የአለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር \FIFA\ በሚያዘው መሰረት ከየትኛውም ውድድር በፊት የጤና ምርመራ ማድረግና መስፈርቱን ማሟላት አለባቸው በሚለው መሰረት በሜዳላይ የሚገጥመውን ጉዳትና ለህይወት አስጊ የሆነ ድንገተኛ አደጋ ለመቀነስ የሚረዳ ነው፡፡
ይህን ምርመራ ማድረግ በዋነኝነት የሚጠቅመው ክለቦችንም ተጫዋቾችንም ነው ተጫዋቾች መጫወት የሚያስችላቸው የጤና ደረጃ ላይ እንደሆኑ ማረጋገጥ እና በዘህ ሂደት የተሟላ የተጫዋቾች የጤና መረጃ በተደራጀ መልኩ እንዲኖር የሚያደርግ ሲሆን የእያንዳንዱን ተጫዋች የጤና ሁኔታ ለመከታተልም ይጠቅማል፡፡

ክለቦች የተዘጋጀውን የጤና ምርመራ ቅፅ\ፎርም ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በመውሰድ ለተጫዋቾቻቸው በህጋዊ የጤና ተቋም ምርመራ ማድረግ የሚገባቸው ሲሆን ህጋዊ የጤና ምርመራ ሰርተፊኬት ይዞ የማይመጣ ክለብም ሆነ ተጫዋች ውል ለማደስም ሆነ ዝውውር ለመፈፀም የማይችልና ውሉ የማይፀድቅ መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የህክምና ክፍል ዳይሬክተር ዶ/ር ሳሙኤል የሺዋስ ገልፀዋል፡፡ አክለውም ይህ አሰራር በከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊግ ክለቦች በቀጣይ እንደሚተገበርም አሳውቀዋል።

ዶ/ር ሳሙኤል የሺዋስ

 

@ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን