ዜናዎች

# የጋቶች ፓኖም የአሜሪካ ቆይታው ታውቋል !

በአሜሪካው ሃርትፎርድ አትሌቲክስ ክለብ የአስር ቀናት የሙከራ ዕድል አግኝቶ የነበረውና ከዋልያዎቹ ተለይቶ እዛው የቀናቶች ቆይታ ያደረገው ጋቶች ፓኖም በከፊል ከተሳካ የአጭር የሙከራ ቀናት በኋላ ወደ ሀገሩ ይመለሳል። በዚሁ ክለብ ቆይታው አጥጋቢ የሚባል ጊዜ በማሳለፍ በክለቡ አሰልጣኞች ዕይታን ማግኝቱን ለኢትዮኪክ ቅርበት ያላቸው ታማኝ ምንጮች ጠቁመዋል።
እንደ መረጃው ከሆነ ጋቶች በቀጣይ ከክለቡ ጋር የሚያቆየውን ምንም ዓይነት ስምምነቶች አለመፈፀሙ የተሰማ ሲሆን ምክንያቹ ደግሞ የHartford Athletic ክለብ እየተካሄደ ባለው እና 10 ጨዋታዎች በቀሩት የአሜሪካው ሁለተኛ ዲቪዚዮን በቀሩት የውድድር ጊዜያት የተጫዋችነት የስራ ፈቃዱን ለማግኘት በሚወስደው ጊዜ ገደብ ጋር እና ተያያዥነት ባላቸው ምክንያቶች ለጊዜው ማስፈረም አለመስፈለጋቸው ታወቋል።
በዚህም ክለቡ ለጋቶች በቀጣይ ዓመት ወይም በአዲሱ የውድድር ዓመት ተመልሶ በመምጣት ከክለቡ ጋር በቂ የዝግጅት ጊዜ በማድረግ አዲስ የሙከራ እና ቀጣይ የስምምነት ሂደቶች እንደሚያካሄዱ መግለፃቸውን መረጃው ይጠቁማል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዜና በቀድሞው የእንግሊዝ እና የማንቼስተር ዩናይትድ እውቅ ተጫዋች በነበረው በዋይኒ ሩኒ እየሰለጠነ በሚገኘው የDC United ክለብ በተመሳሳይ መልኩ የሙከራ ዕድሉን በቀጣይ የውድድር ዓመት መጀመሪያ ላይ ለጋቶች ለመስጠት መፈለጋቸው ተሰምቷል።
ከፈረረኞቹ ጋር የኮንትራቱ ዘንድሮ የተጠናቀቀው ጋቶች ፓኖም በቀጣይ ሳምንታት ወደ ሀገሩ በመመለስ በአገር ውስጥ ለአጭር ጊዜ የሚያስቆየውን ውል ለመፈፀም የሚያስችል ሁኔታዎችን እያሰበ እንደሚገኝ የዚህ ዜና ምንጮቻችን ለኢትዮ ኪክኦፍ አሳውቀውናል።
ኢትዮኪክም ይህንኑ የጋቶችን ማረፊያ የሆነውን ክለብ ለውድ አንባቢዎቿ በቀጣይ እንደምታስነብብ ለማሳወቅ ትወዳለች።