በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከሐምሌ 10 እስከ 25/2013 ዓ.ም ድረስ በዘጠኝ የሴካፋ አባል አገራት መካከል በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የሚካሄደው ከ23 ዓመት በታች የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገራት ውድድር ዛሬ ተጀምሯል።በመክፈቻ ጨዋታው ከረጅም ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ብሔራዊ ቡድኖች በምስራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታቸውን አድርገው በአቻው ውጤት ፈፅመዋል።
የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች በመክፈቻው ጨዋታ በ12ኛ ደቂቃ በኢትዮዽያ ቡናው ዊሊያም ሰለሞን ቀዳሚ የምታደርገውን ጎል አስቆጥሯል። ከጎሉ መቆጠር በኃላ የኤርትራ ቡድን በዓሊ ሱሊማን ተደጋጋሚ ሙከራዎች አድርጓል።
የኤርትራው 10 ቀጥር ዓሊ ሱሌማን በ38ኛው ደቂቃ በኢትዮዽያ የተከላካይ ክፍል ስህተት የተገኘውን አጋጣሚ ወደ ጎል ለውጦታል። የመጀመሪያው አጋማሽ ከመጠናቀቁ በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው አቡበከር ናስር የመጀመሪያ ኳስ ቢስተውም የመሰመር ዳኛው አቋቋሙ ትክክል ይደለም በማለታቸው አቡበከር ናስር ድጋሚ የፍፁም ቅጣት ምቱን በመምታት ወደ ጎል ለውጦታል።
ይሁንና ከአቡበከር ጎል መቆጠር በኃላ ብዙም ሳይቆይ በ44ኛው ደቂቃ የኤርትራ ኮከብ ዓሊ ሱሌማን ሁለተኛውን ለሀገሩም በግሉም አስቆጥሮ የመጀሪያዉ አጋማሽ በ2 ለ 2 አቻ ውጤት ተጠናቋል።የሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች ቀድሞ ጎል ለማስቆጠር ሙከራዎችን አድረገዋል። በተመሳሳይ የጨዋታ እንቅስቃሴ ጨምሮ የቀጠለው ጨዋታ በ58ኛው ደቂቃ የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር ለኢትዮጵያ የመሪነቱን ጎል ማስቆጠር ችሎ ነበር። በዕለቱ ጨዋታ ኮከብ የነበረው የኤርትራው ዓሊ ሱሌይማን በጨዋታው ላይ የመጀመሪያ ሐትሪክ መሥራት ችሏል። ተጨዋቹ ለአገሩም ለግሉም ሦስተኛውን ጎል በ71ኛው ደቂቃ በማስቆጠር ጨዋታው በሁለቱ አገሮች የ3 ለ 3 ዠአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ፎቶ@EFF