በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በ9 ደረጃ የሚገኘው እና በዘንድሮ የውድድር አመት ባደረጋቸው 10 ጨዋታዎች 4 አሸንፎ በተመሳሳይ 4 ተሸንፎ 2 ጨዋታ በአቻ ዉጤት ያጠናቀቀዉ ኢትዮጵያ ቡና በሀድያ ሆሳዕና 1ለ0 መሸነፉን ተከትሎ ዘንድሮ በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ቦታ ዋና አሰልጣኝ ያደረገውን አሰልጣኝ ተመስገን ዳናን አሰናብቷል።
ክለቡ ዛሬ የስንብት ደብዳቤው ጋር በተመለከተ አሠልጣኝ ተመስገንን ያሸጋግረዋል። ኢትዮኪክ አሰልጣኙ ከክለቡ ጋር ዛሬ ከሚኖራቸው የስንብት ደብዳቤ ውውይት በፊት አጭር ቆይታ አድርጋለች።
ኢትዮ ኪክ:- ከኢትዮዽያ ቡናን ክለብ መሠናበትህ ይፋ ሆኗል፣ አሰልጣኝ ተመስገን በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላል?
አሰልጣኝ ተመስገን:– ከኢትዮጵያ ቡና ስለመለያየቴ በይፋ በደብዳቤ የተነገረኝ ነገር የለም ። ነገር ግን በስምምነት የመለያየት ጥያቄ ቀርቦልኝ በስምምነቱ ይዘቱ ላይ በእኔ በኩል ያሉት ጥያቄዎች ስላልተስማማው Hold አድርጌዋለው።
ኢትዮ ኪክ:- ያልተስማማህበት ጉዳዮች ምን ምን ናቸው ?
አሰልጣኝ ተመስገን:- እንደሚታወቀው ከክለቡ ጋር ውላችን የሁለት ዓመት ነበር። ስለዚህ ስንብት የተባለው ውሳኔ እንደ ክለብ በደብዳቤ ወይሞ ይፋዊ በሆነ መልኩም የተገለፀ አይደለም ። ከዛ ውጭ በስምምነት የሚለውን በእኔ በኩል በትክክለኛው የሚገባኝን ጥቅማ ጥቅሜ እና ደሞዜን ላይ ያለውን ስምምነቶች ያላካተተ በመሆኑ አልተቀበልኩትም ፣ነገር ግን ዛሬ በዚህ ጉዳይ ለመነጋገር ቀጠሮ ይዘናል።
ኢትዮ ኪክ:- ከክለቡ ጋር በአጭር ጊዜ ለመለያየት በአንተ በኩል ምክንያት የምትላቸው?
አሰልጣኝ ተመስገን:- የክለቡ ውሳኔ ነው ያንን ማወቅ አልችለም ፣ ነገር ግን በአጭር ጊዜ ይህን አይነት ውሳኔ በወሰዱ በእውነቱ አስከፍቶኛል። ለማንኛውም ነገር አሰልጣኝ ጊዜ ያስፈልገዋል። አሰልጣኝ በወረቀት ያሰፈረውን ሃሳቡን መሬት ላይ ለማወረድ ጊዜ ያስፈልገዋል። አሰልጣኞች በተሸነፍን ቁጥር የምንሰናበት ከሆነ በሊጉ ላይ አንድም አሰልጣኝ አይቀርም ማለት ነው። በተለይ በተለይ ኢትዮጵያ ቡና በእኔ ዞር ማለት የሚያሸንፍ ከሆነ ከክለቡ የሚበልጥብኝ ነገር የለምና ያንን እቀበላለሁ።
ኢትዮ ኪክ:- ኢትዮጵያ ቡናን አሰልጣኝ ተመስገን ከተረከበ በኋላ በዋናነት ሰራው የሚለው ነገሮች ምንድናቸው ?
አሰልጣኝ ተመስገን:- እኔ ለኢትዮዽያ ቡና አደረኩት የምለው ክለቡ በፊት በዲሲፕሊን ይታማ ነበር ያንን የማፅዳት ስራ ሰርተናል። ሌላው ግን በዋናነት 23 አዳዲስ ተጨዋቾች ወደ ክለቡ እንዲቀላቀሉ አድርጊያለሁ። ወጣቶቹ የቡድኑን የወደፊት ተስፋን ይወስናሉ ብዬ ያመንኩባቸውን ተጫዋቾች ላይ መሠረታዊ ስራዎች እየሰራን ነበር።
ኢትዮ ኪክ:- ለክለቡ ውጤት ማጣት ምክንያትስ የምትችለው?
አሰልጣኝ ተመስገን:- አብዛኞቹ ወጣት እና አዲስ ተጨዋች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ የቡድኑ ተጨዋቾች በpre-season ሰዓት ለብሔራዊ ቡድኑ ከቡድኑ ጋር አልነበሩም ። ቡድኑን ለመስራት ጊዜ ያስፈልጋል። ከዛ ውጭ ግን በሊጉ ጨዋታዎች በባህርዳር ሜዳ በነበረው ቆይታ ጥሩ ነበርን ። ድሬዳዋ ከመጣን በኋላ ነው ውጤት ማሳካት ያልቻልነው ለዚህ ምክንያት የሆነው የድሬዳዋ ሜዳው ለውጤት ማጣታችን ተፅዕኖ አለው።
ኢትዮ ኪክ:- ለኢትዮጵያ ቡና ውጤት ማጣቱ የድሬደዋ ሜዳ ምክንያት ነው እያልከኝ ነው ?
አሰልጣኝ ተመስገን:- አዎ። ኢትዮጵያ ቡና ብቻ ሳይሆን አብዛኞቹ ክለቦች ከባህርዳር ወደ ድሬዳዋ ሜዳ ከመጡ በኋላ በሜዳው ምክንያት ውጤት ማሳካት አልቻሉም። እንደምሳሌ ልጠቅስልሽ እችላለሁ ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ በድሬዳዋ 8 ነጥብ ጥሏል ፣ እኛ 11 ነጥብ ፣ መከላከያ 4;፣ ሃዋሳ እና ሌሎችም እንዲሁ፣ አብዛኞቹ 98% በባህርዳር ስኬታማ የነበሩ ክለቦች ጥሩ መሆን አልቻሉም። ይሄ ደግሞ የድሬዳዋ ሜዳ ምቹ አልነበረም ።በአጠቃላይ በእኛ በኩል በባህርዳር ሜዳ ኳስ ይዘን በመጫወት ስኬታማ ነበርን የድሬደዋ ሜዳ ለውጤቱ ሜዳው ተፅኖ ፈጥሮብናል እላለሁ።
ኢትዮ ኪክ:- በቀጣይ የአሰልጣኝ ተመስገን ምን ያስባል?
አሰልጣኝ ተመስገን:- ከሁኔታዎች ጋር ህይወት ይቀጥላል። ወደፊት በተመሳሳይ መልኩ በአሰልኝነት ሙያ በሌላ ክለብ እቀጥላለሁ።
ኢትዮ ኪክ:- በመጨረሻ ለኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች የምትለው ካለ?
አሰልጣኝ ተመስገን:- የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በጣም ክለባቸውን የሚወዱ ደጋፊዎች ናቸው። በተለይ በተለይ ክለባቸው ሻምፒዮና ሆኖ ማየት ለሚፈልገው ደጋፊ ያንን አሳክቼ ቢሆን ኖሮ በጣም ደስተኛ ሆን ነበረ።