ዜናዎች

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በሴካፋው ሻምፒዮና ላይ ትውልደ ኢትዮጵያን ለማካተት የቡሩንዲን ታላቅ ተሞክሮ ዕውን ሊያደርጉ ነው!

የምስራቅ እና መካከለኛው ሀገራት ከ23 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ከሰኔ 26/2013 እስከ ሐምሌ 11/2013ዓ.ም በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በባሕር ዳር ከተማ ይካሄዳል።በዚህ ውድድር ተሳታፊ የሆነው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ  ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጨዋቾችን በተመለከተ ታላቅ እና ሲጠበቅ የነበረውን ሃሳብ ተግባራዊ ሊያደርጉ መሆኑ ተሰምቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከአፍሪካም ሆነ ከሌሎች ዓለማት በውጭ የሚገኙ ተጨዋቾችን ለብሔራዊ ቡድኑ ባለመጠቀም ቀዳሚ አገር ነው። ለዚህ ደግም የሁለት ዜግነት ፍቃድ ሁልጊዜ እንደ ችግር ይነሳል። ይሁንና ፊፋ የሁለት ዜግነት ፍቃድ ለማይቻልበት ሀገራት ( Sport Passport) አምጥቷል። ሆኖም ይንን ተግባር በትክክል ለፊፋ የሚጠይቅ እና የሚያስፈፅም ባለመኖሩ ሁልጊዜም ችግሩ የዜግነት እንደሆነ ተደርጎ ይገራል።
ነገር ግን አሁን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና የፌዴሬሽኑ  ፀሐፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን የቡሩንዲ ብሔራዊ ቡድን ያደረገውን መልካም   ተግባር  በኢትዮጵያ ለመተግበር ፍላጎታቸውን ማሳየታቸው ተሰምቷል። የቡሩንዲ እግርኳስ ፌዴሬሽን በትላንትናው ዕለት ቁጥራቸው 20 የሚሆኑ በአሜሩካ፣ በአውሮፓ እና በተለያዩ አገራት የሚገኙ ትውልደ ቡሩንዲያዊያን ተጨዋቾችን ለብሔራዊ ቡድኑ ጥሪ አቅርበው ከቡድኑ ጋር ቀላቅለዋል።
የቡሩንዲ እግርኳስ ፌዴሬሽን እንዳስታወቀው በኢትዮጵያ ለሚዘጋጀው ከ23 ዓመት በታች የሴካፋ ዋንጫ ለመምረጥ ከውጭ ሀገር የመጡት 20 ተጨዋቾች ከአገሩ ውስጥ ቀድመው ከተመረጡት ተጨዋቾች ጋር የተቀላቀሉ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ጥሩ ብቃት እና የተሻለ ብቃት ያላቸው ተጨዋቾች ለሴካፋው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና እንደሚመረጡ አስታውቋል።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በበኩላቸው የቡሩንዲን ብሔራዊ ቡድንን ተሞክሮና መልካም ተግባር በተወሰነ መልኩ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመተግበር በውጭ የሚገኙ ተጨዋቾን በቡድኑ ለማካተት ፍላጎታቸው መሆኑ ታውቋል። ይህንንም ለማሳካት ይረዳ ዘንድ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ  እና ፌዴሬሽኑ  በውጭ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ጋር አብሮ ለመሥራት የመጀሪያዉ ምዕራፍ ላይ መሆናቸው ታውቋል። በተለይም በጀርመን የሚገኘውና ለበርካታ ጊዜያት የውጭ ተጨዋቾች በብሔራዊ ቡድኑ እንዲካተቱ በሙያው የስካውቲንግ ስራ ለመስራት ሁሌም ፍላጎቱ ከሆነው የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኑና የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋች ዴቪድ በሻህ ጋር በጥምረት ለመስራትና አዲስ ነገር ለመተግበር ማሰባቸው ተሰምቷል።
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በአሁን ሰአት ከዴቪድ በሻህ ጋር በ Zoom የሚገናኙ ሲሆን በዴቪድ በኩል በአውሮፓ የሚጫወቱ እና አሁን የኢትዮጵያ ፓስፖርት ያላቸውን  ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጨዋቾች ለሴካፋ የሚካተቱበትን ሂደት ለመፍጠር አስቀድሞ የተጨዋቾች መረጃ የመሰብሰብ ሂደቱን የጨረሰ ሲሆን ተጨዋቾቹ ከኢትዮጵያ ከተመረጡት ተጨዋቾች ጋር በመጫወት እንደ ቡሩንዲ ቡድን የተሻለውን የመመምረጥ ሂደት እንደሚደረግ መታሰቡ ታውቋል።
የውጭ ተጨዋቾችን በኢትዮጵያ የማካተት ተግባር በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እንዲሁም በፌዴሬሽኑ  መታሰቡ ታላቅ ለውጥ ሲሆን ከውጭ የሚመጡት ተጨዋቾች ከአገር ውስጥ ተጨዋቾች ጋር በመጫወት የተሻለው የማግኘት ሂደቱ  መታሰቡ  አሁን ባይሳካ እንካ በቀጣይም   ይኸም ተግባር ሊቀጥል ይገባል።