ዜናዎች

ብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅቱን ቀጥሏል – ሱራፌል መጠናኛ ጉዳት አስተናግዷል !

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቀጣይ ሳምንት ለካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ የማለፉ አልያም የመውደቁ የመጨረሻዎቹ ውጤቶች የሚታወቁበት ነው። ብሔራዊ ቡድኑ የፊታችን ዕሮብ መጋቢት 15 ቀን በባህር ዳር ዓለም አቀፉ ስታዲየም ከማዳጋስካር ጋር ከሚያደርገው ጨዋታ በተጨማሪም በስድስት ቀን ልዩነት መጋቢት 21 ኮትዲቯር ጋር አቢጃን ተጉዘው ይገጥማሉ።ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሊግ ውድድሮች ሳይቋረጥ የብሔራዊ ቡድን ዝግጅት መጀመራቸው ይታወሳል። የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ወደ ጅማ ከመጓዙን ተከትለው ለተጨዋቾቹ አጭር የቅድመ ትውውቅ ዝግጅት ማድረጋቸው ይታወሳል። በወቅቱም የቀናት ትውውቅ አስቀድመው ማድረጋቸው ከዚህ ቀደም የነበረውን አካሄድ በተወሰነ መልኩ ያቃለለም እንደሆነ ሲነገር ተደምጧል ። ከጅማው የመጀመሪያው አጭር የትውውቅ-የዝግጅት ምዕራፍ ቀጥሎ ቡድኑ ዋነኛ የዝግጅት የሆነው ሁለተኛ ምዕራፍ ከቀናት በፊት በጠሩት 28 ተጫዋቾች መጀመራቸው እና ብሔራዊ ቡድኑ ከትላንት በስቲያ በወዳጅነት ጨዋታ የማላዊ አቻውን 4 ለ 0 ማሸነፉም አይዘነጋም። ብሔራዊ ቡድኑ ከወዳጅነት ጨዋታው መልስ ዛሬ የሁለተኛ ቀን ልምዱን አድርጓል። ከማላዊ በነበረው የወዳጅነት ጨዋታው ላይ መስኡድ መሀመድ ፣ ጌታነህ ከበደ ፣ሱራፌል ዳኛቸው እና አቡበከር ናስር ለዋልያዎቹ የማሸነፊያ ግቦችን ያስቆጠሩት እንደነበረም ይታወሳል።በወቅቱ ጎሎቹን ካስቆጠሩት እና በጥሩ አቋም ላይ ከሚገኙት አንዱ የሆነው የፋሲል ከነማው ሱራፌል ዳኛቸው በዛሬው የረፋድ ልምምድ ላይ መጠናኛ ጉዳት አስተናግዷል። ይሁንና የሱራፌል ጉዳቱ መጠነኛ በመሆኑ ከቡድኑ ጋር ልምምዱን መቀጠሉን እና ማካሄዱ ሲታወቅ በአሁኑ ሰአት በብሔራዊ ቡድኑ ላይ ሁሉም ተጨዋቾች ሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።