ቤትኪንግ ፕሪሜር ሊግ የ2013 ሊጎች እና ውድድሮች

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2015 13ኛ ሳምንትና የዲሲፕሊን ውሳኔዎቹ !

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2015 13ኛ ሳምንት በተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች አራት ጨዋታዎች በመሸናነፍ አራት ጨዋታ በአቻ ሲጠናቀቁ 20 ጎሎች በ18 ተጫዋች ተቆጥረዋል። የጎሎቹ አገባብ ሁለት በፍፁም ቅጣት ምት ቀሪዎቹ በጨዋታ የተቆጠሩ ናቸው። በሳምንቱ 36 ተጫዋቾችና የቡድን አመራሮች በቢጫ ካርድ ሲገሰፁ የተመዘገበ ቀይ ካርድ የለም።
የኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ አርብ ታህሳስ 14 2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያ(ዎች)ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
በተጫዋቾች ፍሬዘር ካሳ(ሀዲያ ሆሳዕና)፣ ፣ ይገዙ ቦጋለ(ሲዳማ ቡና) እና አሰጋኸኝ ጴጥሮስ(ድሬደዋ ከተማ) በተለያዩ 5 የክለባቸው ጨዋታዎች የቢጫ ማስጠንቅቂያ ካርድ በመመልከታቸው እያንዳንዳቸው በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 1500 /አንድ ሺ አምስት መቶ/ እንዲከፍሉ ተወስኗል። በተጨማሪም ኤፍሬም አሻሞ(ሀዋሳ ከተማ) ክለቡ ከወላይታ ድቻ ጋር ባደረገው የ13 ኛ ሳምንት ጨዋታ ሃይማኖታዊ መልእክት የሚያስተላልፍ ምስል በውስጥ ልብሱ ደርቦ ስለመልበሱና ስለማሳየቱ ሪፖርት የተደረገበት ሲሆን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ደንብ መሰረት ተጫዋቹ የገንዘብ ቅጣት ብር 3000 /ሶስት ሺህ ብር/ እንዲሁም ክለቡ የገንዘብ ቅጣት ብር 10000 /አስር ሺህ ብር/ እንዲከፍል ውሳኔ ተላልፏል።
አቶ ቾምቤ ገ/ህይወት (የቡድን መሪ – ሲዳማ ቡና) ክለቡ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር በነበረው የ 13ኛ ሳምንት ጨዋታ ቅድመ ስብሰባ ወቅት ከ15 ደቂቃ በላይ ዘግይተው ስለመምጣታቸው ሪፖርት የቀረበባቸዋል መሆኑ የቡድን መሪው ለፈፀሙት ጥፋት በፕሪምየር ሊግ የውድድር ደንብ መሰረት ብር 1000/አንድ ሺህ/ እንዲከፍሉ ተወስኗል።