የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ከቀናት በፊት ጥሪ ያቀረቡላቸውን 26 ተጨዋቾችን ይዘው ዋልያዎቹ ዝግጅት ሲያደርጉበት በነበረው የካፍ የልህቀት ማዕከል ዛሬ ረፋድ ሉሲዎቹም ዝግጅታቸውን ጀምረዋል።ኢትዮጵያ በሴቶች ብሄራዊ ቡድን በቀጣይ ላለበት የሴካፋና የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የተጨዋቾች ምርጫ አጠናቀው ዛሬ የመጀመርያ ልምምዳቸውንም አከናውነዋል።አሰልጣኝ ብርሃኑ የቀድሞ ረዳት አሰልጣኝ የነበረችውን መሠረት ማኔኝ አሰናብተው የባህር ዳር ከተማን ወደ ሊጉ ያሳደገችው ሰርክአዲስ እውነቱ ሞክትላቸው አድርገው ሾመዋል ።
በአንፃሩ በተጨዋቾች ምርጫ ላይ አሰልጣኝ ብርሃኑ የ2013 የኢትዮዽያ የሴቶች ሊግ ኮከብ ተጨዋች እና የዘንድሮው የሊጉ ሁለተኛ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ የነበረችውን የንግድ ባንኳን ረሂማ ዘርጋውን አለማካተታቸው አነጋጋሪነቱ ቀጥሏል።እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከሚጠብቀው ዋናው ውድድሮች በፊት ከሚያዝያ 2 – ሚያዚያ 5 ባሉት ቀናት ከደቡብ ሱዳን ጋር የወዳጅነት ጨዋታ የሚካሄድ መሆኑ ፌዴሬሽኑ ከቀናት በፊት ማሳወቁም ይታወሳል።